2004 ኢትዮጵያ ታላላቅ ሰዎቿን ያጣችበት ዓመት
ጊዜው በጣም ይነጉዳል፡፡ ትናንት የጀመርነው 2004 ዓ.ም ዛሬ ተጠናቋል፡፡ አንድ ዓመት እንደቀልድ እልም ይላል፡፡ መስከረም አልፎ መስከረም ሲተካ ሁሉም በየእምነቱ ለፈጣሪ እራሱን አደራ ይሰጣል፤ ‹‹ዓመት ከዓመት በሰላም አሸጋግረን›› ሲል፡፡ የተፈቀደላቸው ሲሻገሩ ያልተፈቀደላቸው ደግሞ ዓመቱን ሳይሻገሩ ይቀራሉ፡፡ ይህ የተፈጥሮ ዑደት ነው እና እንዲህ እያለ በያመቱ ይቀጥላል፡፡ ማንም ከሞት የሚቀር የለምና፡፡ ባጠናቀቅነው 2004 ዓ.ም ኢትዮጵያ ታላላቅ ሰዎቿን አጥታለች፡፡ ያሳለፍነው ዓመት ወጣት ጋዜጠኞችንም ወስዶብናል፡፡ በየሁለት ወሩ እና በየሦስት ወሩ አንዳንዴም በአንድ ወር ውስጥ የሁለት ታላቅ ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ገና በመስከረም ወር የተጀመረው ሐዘን እስከ ነሐሴ ዘልቋል፡፡ አንጋፋው ተርጓሚ፣ ጋዜጠኛና ደራሲ ማሞ ውድነህ እና አንጋፋው ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት፡፡ ኢትዮጵያን ለ21 ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሩት መለስ ዜናዊ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ለ20 ዓመታት የመሩት አቡነ ጳውሎስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በጥቂት ቀናት ልዩነት ነው ሕይወታቸው ያለፈው፡፡ የእውቅና ታላላቅ ሰዎች ተከታትሎ ማለፍ የተነሳም ከዐይን የራቀ እና የታመመ ሰው ሁሉ ‹‹ሞተ›› እየተባለ ወሬ ሲናፈስበት የዘለቀ ዓመት ነበር- 2004 ዓ.ም፡፡ አርቲስት አስናቀች ወርቁ (1927-2004) በተጠናቀቀው የኢትዮጵያውያን 2004 ዓ.ም የመጀመሪያ ሣምንት ከግማሽ ምእት ዓመት በላይ በክራር ቅኝቷ የብዙዎችን ቀልብ ገዝታ የኖረችው አስናቀች ወርቁ ኅልፈተ ሕይወት የተሰማበት ወር ነበር፡፡ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር (በአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) በታላላ