የኑሮ ውድነት ያሸበበው የበዓል ዋዜማ
በታደሰ ገብረማርያም “የተለያዩ ዓይነት የምግብ ሸቀጦችና የእርድ እንስሳት ሥጋ ዋጋ ከአቅም በላይ ሆኗል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ገንዘብ የመግዛት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ሲሔድ እንጂ ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር ሲጣጣም አይታይም፡፡ በዚህም የተነሳ በክርስቲያንና በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ዘንድ የሚከበረውን የዘመን መለወጫን የሚያክል ታላቅ በዓል በጥሩ ዝግጅት ለማሳለፍ ቀርቶ የዕለት ፍጆታን ለመሸፈን በማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታም በደሀና በሀብታም መካከል ያለው ክፍተት ከመጥበብ ይልቅ እየሰፋ መምጣቱን ለማወቅ የግዴታ የኢኮኖሚ ባለሙያ መሆን አይጠይቅም፡፡” ይህንን አስተያየት የሰነዘሩት በተለያዩ የገበያ ሥፍራዎች ለዘመን መለወጫ በዓል ቅቤና ዘይት፣ ዶሮ፣ በግ፣ እንቁላል፣ የጤፍና የስንዴ ዱቄት ሲሸምቱ ካገኘናቸው ወገኖች መካከል አንዳንዶቹ የበዓሉን ዝግጅትና የገበያውን ሁኔታ አስመልክተው በየተራ በሰጡት ማብራርያ ነው፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ አባባል ከሆነ በተለይ በምግብ ሸቀጦች ላይ የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ ነጋዴዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ አሻጥር ከሚፈጽሙባቸውም የምግብ ሸቀጦች መካከል የምግብ ዘይትና ቅቤ፣ በአባይ ሚዛን የሚቸረችሩት ጥራጥሬዎችና የእህል ዱቄት፣ ሥጋ የመሳሰሉና ሌሎችም እንደሚገኙበት ጠቁመው ይህንን የሚከታተልና የሚቆጣጠር መንግሥታዊ አካል መኖሩን በመገናኛ ብዙኅን እንደሚሰሙ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አካል በስም እንጂ በገቢር እንደማይታይና በአሻጥረኞችም ላይ ዕርምጃ ሲወስድ እንዳልተሰማ ወይም እንዳልታየ ነው ያስረዱት፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ነዋሪ የሆኑና መርካቶ ቅቤ ተራ ያገኘናቸው ወይዘሮ ሐረገወይን አበበ “ኑሮዬ መካከለኛ