የመለስ ኢትዮጵያና ወራሾቿ
ፎቶ ኢንተርኔት በሰለሞን ጎሹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባረፉ በሁለት ሳምንታቸው ግብዓተ መሬታቸው ተፈጽሟል፡፡ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ መንገዶች ሐዘን ከመግለጽ ጋር በተያያዙ እንቀስቃሴዎች ተወጣጥሮ የነበረው መንግሥት ወደ መደበኛው ሥራው እንደሚመለስ ይጠበቃል፡፡ የሥራዎቹ ሁሉ መጀመርያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲመርጥ ወይም የተመረጠውን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲያፀድቅ ማድረግ ነው፡፡ በቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ ዙሪያ እየተደረጉ ያሉት የሐሳብ ልውውጦች ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የግል ሰብዕናና የፖለቲካ አመራር ብቃት፣ ከኢሕአዴግ የፖሊሲ ለውጥ የማምጣትና ያለማምጣት ጥያቄ፣ ከፓርቲ ፖለቲካውና ከዓለም አቀፍ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ባለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያን በፈለጉት መንገድ የቀረጿት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የአገሪቱን ፖሊሲዎች በመንደፍ፣ አመራራቸውን ማዕከላዊ በማድረግ፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ነጥረው በመውጣታቸው የተነሳ የተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሥራ ከማክበዳቸውም በላይ፣ ኢትዮጵያውያን፣ የውጭ ዜጎችና መንግሥታት በቀጣይ ሥራዎች ላይ ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓል፡፡ የመለስ የአመራር ዘዬ መለስ ከልጅነታቸው ጀምሮ ብልህና ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ ስለእሳቸው የተጻፉ ሰነዶች ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ በአድዋም ሆነ በአዲስ አበባ ዊንጌት ትምህርት ቤት ያሉ መዛግብትም ይህን ያስተጋባሉ፡፡ ያቋረጡትን የሕክምና ትምህርትም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩም ጉብዝናቸው ተከትሏቸዋል፡፡ የ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውና ከዩኒቨርሲቲ ተማሪነታቸው ጋር አብሮ በመሄዱ፣ የንባብ ፍላጎታቸው ከመደበኛው የትምህርት ጥናት ውጪ ወደ ፖለቲካው እንደተሸጋገረ ይ