የኢትዮጵያን የውክልና ሕግ ቢያውቁ ይጠቀማሉ
በኤልያስ ዶጊሶ ከደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ እጅግ እየዘመነ በመጣው የዓለማችን የኑሮ ሁኔታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሕልውና ጥያቄ ሆኗል። በተለይ ሕዝቦች ከከፋ ድህነት ተላቅቀው የተሻለ ሕይወት መምራት እንዲችሉ በኢኮኖሚው መስክ ንቁ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡ እንደ ንግድ ያሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ደግሞ አንዳንዴ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት የተለያየ ስፍራ መገኘትን ይጠይቃል። የሰው ልጅ ደግሞ በተፈጥሮው በጊዜና በቦታ ውሱን ከመሆኑ አንፃር በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት ጥቅሙን በሚመለከቱ ስፍራዎች ሁሉ ተገኝቶ ተግባሩን መከወን አይችልም፡፡ እነዚህ መሰል ጉዳዮችን አስመልክቶ የሰው ልጅ የሚኖረው ብቸኛ አማራጭ እንደራሱ ሆኖ በእርሱ እግር ተተክቶ ጉዳዮቹን ወይም ሥራዎቹን የሚከውንለትን ሰው መወከል ግድ ይሆንበታል፡፡ ሥራዎችን በውክልና ማሰራት አስፈላጊ የሆነው በኢኮኖሚው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ የሕይወት መስክም ካለው ጠቀሜታ አኳያ ነው፡፡ በየትኛውም ዘርፍ የሚደረጉ የውክልና ውሎች ማዕቀፋቸው በፍትሐብሔር ሕግ ከአንቀጽ 2179 እስከ 2285 ባሉ ድንጋጌዎች ነው፡፡ በዚሁ ሕግ መሠረት የውክልና ሕግ የእንደራሴነት ሕግ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሁለቱንም ቃላት መጠቀም በፍቺ ረገድ ልዩነት የላቸውም፡፡ በአማርኛ መዝገበ ቃላት «ወኪል» የሚለውን ቃል እንደዋና ሆኖ የሚሰራ፣ ተጠሪ፣ ኃላፊ፣ ዋናውን ተክቶ እንዲሰራ የተመረጠው ሰው፣ አካል የሚል ሲሆን «ውክልና» ማለትን ደግሞ ለአንድ ሰው ወይም ድርጅት ወኪል፣ ተጠሪ መሆን የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል፡፡ በፍ/ሕ/ቁ 2199 መሠረት ደግሞ «ውክልና» ማለትን በሚከተለው መልኩ ይተረጉመዋል፡፡ «ተወካይ የተባለ አንድ ሰው ወካይ ለተባለው ሰው እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ሕጋዊ ሰራዎችን በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ነው።