የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
አዲስ አበባ ነሐሴ 15/2004 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ የሚኒትሮች ምክር ቤት ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አገራችንን ላለፉት 21 ዓመታት በከፍተኛ ብስለትና ብቃት ሲመሩ የቆዩት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ካደረባቸው ሕመም ለመፈወስ በውጭ አገር በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 5፡40 በድንገት ማረፋቸውን ለመላው የአገራችን ሕዝቦች በታላቅ ሐዘን ይገልጻል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላለፉት ሁለት ወራት በህክምና ሲረዱና በጤናቸው ላይ መሻሻል ሲታይ ከቆየ በኋላ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በተከሰተ ድንገተኛ ኢንፌክሽን እንደገና ሕመማቸው ተባብሶ ለአስቸኳይ የህክምና እርዳታ ወደ ሆስፒታል ገብተው በህክምና ሙያተኞቻቸውም እገዛ ቢደረግላቸውም በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 5፡40 ሲሆን ህይወታቸው ሊያልፍ ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነትና በታማኝነት አገራቸውን አገልግለው ከፍተኛ የለውጥ ተስፋ ያሳዩንን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እልፈተ ህይወት ሲገለጽ በኃዘን በተሰበረ ልብ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከምንም ነገር በላይ አገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚወዱ ለዚች አገርና ሕዝብ የላቀ ራዕይ የነበራቸው መሪ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራዕያቸውን እውን ማድረግ የጀመረና አስተማማኝ ውጤት ማምጣት የቻለ ድርጅትና መንግሥት የገነቡ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ መጠራት እንድትጀምር ያደረጉ ታላቅና እ