“በክር ሥራ ጀምራ በናይሮቢ ሱቅ የከፈተች የሃዋሳ ወጣት
ፎቶ ኣዲስ ኣድማስ ፍላጐት እውቀትና ሙያ፣ ጉልበትና በራስ መተማመን እንጂ፣ ቤሳ ቤስቲን አልነበራትም፡፡ አንድ የቤትና የቢሮ ቁሳቁስ ማምረቻ ድርጅት ሄዳ ጣውላ በዱቤ እንዲሸጡላት ጠየቀች፡፡ የድርጅቱ ባለቤት ወጣቷ ሴት በድፍረትና በልበ ሙሉነት ባቀረበችላቸው ጥያቄ ቢገረሙም፣ “ከየት አምጥተሽ ልትከፍይኝ ነው? አይሆንም” አላሉም፡፡ “እሺ ውሰጂ” አሏት፡፡ ድርጅቱ የሽመና መሳሪያ አምርቶ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ራሷ የመሸመኛውን፣ የማድሪያውን፣ የምርት መጠቅለያውን ዲዛይን ሠርታና እንጨት ገጣጥማ እያሳየች አሠራች፡፡ ክር መሸጫ ሄዳ በዱቤ፣ የ80 ብር ክር ወስዳ፣ በሽመና መሳሪያው ክሩን ወደ ጨርቅነት ለወጠችው፡፡ ከዚያም ጨርቁን ቆራርጣ መንገድ ዳር አሰፋች፡፡ በገና 1995 በዓል ዕለት ሰባት የሰፈር ሕፃናት ሰብስባ ያሰፋቻቸውን ልብሶች አልብሳ ለቀቀቻቸው - ሳትታዘዝ፡፡ የአራቱ ልብሶች ዋጋ ወዲያው ሲከፈላት ሦስቱ በዱቤ ተሸጡ፡፡ መቶ ብር በማይሞላ የክር ዱቤ ሥራ ጀምራ ዛሬ ከግማሽ ሚሊዮን (500,000) ብር በላይ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማምረቻ መሳሪያዎች ስለተገዙ በደንብ ሂሳብ ከተሠራ ከተጠቀሰው በላይ (ኧረ በግምት ሚሊዮን ሳይደርስ ይቀራል ብላችሁ ነው?) ካፒታል እንዳላት ተናግራለች - ወጣት ዙፋን ኢብራሂም፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ምርቶቿን በምሥራቅ አፍሪካ እያስተዋወቀች መሆኑን ተናግራለች፡፡ በናይሮቢ - ኬንያ አስሊ 10th street እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ምርት ማሳያና መሸጫ ሱቅ መክፈቷን ገልፃለች፡፡ ዙፋን፣ በታንዛኒያም ተመሳሳይ ሱቅ ለመክፈት ሐሳብ እንዳላት ገልፃለች፡፡ ዙፋን፣ ወላጆቼ እኔን ከሙዚቃ ለመለየት ኢትዮ ስዊድሽ ሕፃናትና ወጣቶች ማረሚያና ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ቢያስገቡኝም፣ ዛሬ፣ ኢትዮ ስዊድሽ መተዳደሪያ ሆኖኛል ትላለች፡፡ ም