የቤራ ቢር ድፍራት በሀዋሳ ተወዳጅ ሆኗል
ባለቤቱና የሥራ ኃላፊዎች ከአስተናጋጆች የሚለዩት ዩኒፎርም ባለመልበሳቸው ነው፡፡ በአጭር ታጥቀው በሁሉም አቅጣጫ በንቃት ይቃኛሉ፡፡ እንግዶች ገብተው እንደተቀመጡ፣ ለቦታው የተመደበ አስተናጋጅ፣ ቀድሞ የገባ እንግዳ እየታዘዘ ወይም ትዕዛዙን ለማቅረብ ሄዳ/ዶ ከሆነ እነሱ ጠጋ ብለው ፈገግታ ጋብዘው ትዕዛዝ ይቀበሉና ለምድብተኛው አስተናጋጅ ቦታውን በማመልከት ትዕዛዙን ያስተላልፋሉ፡፡ ይህ ትዕይንት የሚስተዋለው ለሥራም ሆነ ለመዝናናት ሀዋሳ ከተማን የረገጠ ሰው ከኃይሌና ከሌዊ ሪዞርቶች ቀጥሎ ከሚጐበኛቸው ስፍራዎች አንዱ በሆነውና ከአዲስ አበባ ውጭ የቢራ መጥመቂያ ጋኖች በግልፅ እየታዩ ትኩስ ድራፍት በሚጠጣበት ቤራ ቢር አዳራሽ ነው፡፡ “ሰው፣ ድራፍት በጣም ይፈልጋል፡፡ አቅርቦቱ ግን የተሟላ አይደለም፡፡ ዛሬ አንድ፣ ነገ ሦስት ወይም አምስት፣ ከነገ ወዲያ አንድ በርሜል ድራፍት … በቃ እንደተገኘ ይሰጡናል ሰው ደግሞ በአቅርቦት ማነስ ሲቸገር ብዙ ጊዜ አያለሁ፡፡ ይህን ችግር እንዴት መቅረፍ ይቻል ይሆናል? እያልኩ ሳሰላስል፣ “በውጭ አገር እንደ ጎጆ ኢንዱስትሪ ያለ፣ ድራፍት ቢራ መጥመቂያ አይኖርም ይሆን?” አልኩ - ለራሴ፡፡ “ይህን ጉዳይ በሥራ ለተዋወቅኋቸው የ”ሌንቦ” ብስኩት ባለቤቶች አጫወትኳቸው፡፡ እነሱም በመገረም ተያዩና፤ አንደኛው እኛም’ኮ በዚህ ላይ ልንሠራ ተዘጋጅተናል፡፡ ካታሎጉ (የአሠራር መግለጫው) እኔ ጋ አለ፤ እንዴት አሰብከው?” ብሎ ያሰብኩትን ዓይነት ካታሎግ ሲያሳየኝ የደስታ ስሜት ወረረኝ፡፡ “እኔም ያሰብኩት ልክ እንደዚህ ያለ ነው፡፡ በቃ! ቦታ ውሰድና አብረን እንሥራ አልኩት፡፡ እስከዛው እኔም የራሴን ሆቴል አጠናክሬ ስሠራ ቆየሁ፡፡ እነሱ በሌላ ሥራ ስለተወጠሩ ያ የተስማማንበት ሐሳብ ወደ ተግባር ሳይመነዘር ዓመት ሞላው፡፡