ኢሳት “ሰበር ዜና” የሲዳማ ወጣቶች “ሲወን” የሚል አዲስ የህቡዕ ድርጅት ዛሬ በአዋሳ መሰረቱ
ሰኔ ፳፫ (ሃያ ሶስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም ኢሳት ዜና:-የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ የግብርና ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የክልሉ ፖሊስ ተወካዮች፣ የምክር ቤት አባላትና እና ሌሎችም ከ 300 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ዛሬ በአዋሳ ከተማ በህቡእ ተሰባስበው የሲዳማ ወጣቶች ንቅናቄ የሚል ድርጅት መስረተዋል። በጉባኤው ላይ ከ22 ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች የተወከሉ ወጣቶች የተገኙ ሲሆን፣ የትግል ስትራቴጂያቸውን እና አላማቸውን ለተሰብሳቢው ይፋ አድርገዋል። በከፍተኛ ሚስጢር በተካሄደው ጉባኤ ላይ የወጣቱ አመራሮች የሲዳማ ህዝብ ማንነቱን ለማረጋገጥ የሚያደረገውን ትግል ወጣቶቹ ወደ ፊት ለመግፋት መወሰናቸውን የገለጡ ሲሆን ፣ የመጨረሻ ግባቸው ኢትዮጵያን አሁን ከገባችበት ፈተና ለማላቀቅ ትግል ማድረግ መሆኑን ገልጠዋል። የወጣቶቹ አመራሮች የተለያዩ ብሄረሰብ ተወካዮችን ለመጥራት የተገደዱትም አላማቸው አካባቢያዊ ሳይሆን ብሄራዊ አጀንዳ ያለው መሆኑን ለማሳየት ነው ብለዋል። በጉባኤው ላይ የወላይታ ተወካይ ” እኛ ወንድማማች ህዝብ ነን፤ ኢትዮጵያዊነታችን ይበልጣል፣ ሀይለማርያም ደሳለኝ በሰራው ስህተት ወላይታ በሙሉ በሲዳማ የሚጠላበት እና የምንለያይበት ምክንያት የለም ፣ ሀይለማርያም በምንም አይነት መልኩ ወላይታን አይወክልም፤ ስለዚህ በእርሱ አይን ባታዩን፣ አብረን ብንሰራ ይህችን አገር እናሳድጋለን፣ ከገባችብት ችግር እናወጣለን” ብሎአል። የንቅናቄው አመራሮች “የእኛ ትግል የብሄር ጥያቄ አይደለም ፤ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ እና የሌሎች ብሄርና ብሄረሰቦችን ተወካዮችን የጋበዝነውም አላማችን ብሄራዊ መሆኑን ለማሳየት ነው፣ አሁን የሲዳማን ጥያቄ አንስተናል ትግላችን ግን በዚህ አያቆምም፣ አብረን ለኢትዮጵያ ነጻነት እንታገላለን” የሚል መልስ ሰጥተዋል።