ጊዳቦ ፍልውሃ ገና ያልተነካ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም
ቅዱስ ኃይሉ ይርጋለሞች፣ ዳሌዎች እንዲሁም እነዚህን አካባቢዎችና የተለያዩ አገልግሎታቸውን ያዩ ሁሉ ሳይቋደሱት አያልፉም። የጊዳቦ ፍልውሃን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግሥት ሲዳማ ዞን ዳሌ ወረዳ ይርጋለም ከተማ የሚገኘው ይህ የፍልውሃ ቀደም ሲል በዋቢ ሸበሌ ሆቴሎች አስተዳደር ሥር ይተዳደር ነበር። አሁን ደግሞ የሲዳማ ልማት ማኅበር ተቋም ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ እዚህ አካባቢ በሄድኩ ቁጥር እኔም ይህንን ሀብት ሳልቋደስ አልመለስም። በቅርቡም ወደዚሁ ፍልውሃ አገልግሎት ዘልቄ ያለፈውን እያስታወስኩ የአሁኑን አገልግሎቱን ቃኘሁ። ወደፊትም ሊኖረው የሚችለውን አቅምም ተንብያለሁ። የፍልውሃ አገልግሎቱን ተጠቃሚ የሚያደርገውን ትኬት የሚቆርጡበት ቢሮ ቀድሞ ከነበረበት ወደ መግቢያው አካባቢ መጥቷል። ራሱን የቻለ ቤትም የፍልውሃ አገልግሎት መስጫ ቤቶቹ ከራስጌያቸው ያደረጉት ኮረብታውን ጥግ ይዞ ተሠርቶለታል። የፍልውሃ አገልግሎቱ ሁሌም በወረፋ የተጨናነቀ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ቀን ምሳ ሰዓት ላይ ነው ወደ ሥፍራው ያቀናሁት። በእኔ ቤት ብልጥ ሆኜ ቶሎ አገልግሎቱን አግኝቼ ልመለስ። የትኬት መቁረጡ ተራ እስኪደርሰኝ ድረስ ዙሪያ ገባውን ተመለከትኩት። ትኬቱ የሚቆረጥበት ሥፍራ ፍልውሃው የሚገኝበትን አካባቢ በሙሉ ለመቃኘት ያስችላል። ቁልቁል ስመለከት የጊዳቦ ወንዝ ግራ ቀኙን በልምላሜ ታጅቦ በርበሬ መስሎ መፍሰሱን ተያይዞታል። ወቅቱ ክረምት ነውና የውሃው መጠን በጣም ጨምሯል፤ የሚጣደፍ አይመስልም። ድምፁ አይሰማም ከወንዙ ባሻገር የአርሶ አደሮች መንደር፣ እንሰት፣ ዛፎች እና የተለያዩ ተክሎች ይታያሉ። ከነዚህ ተክሎች ውስጥ ቡናና የፍራፍሬ ዛፎች ሊገኙበት እንደሚችሉ ጠጋ ብዬ ያየኋቸው የከተማና የገጠር መኖሪያ ጊቢዎች