ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ
የመንግሥት ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ብሏል የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ለምን ወጣ መባሉ ተገቢ አይደለም - ምርጫ ቦርድ ምርጫ ቦርድ ከኢህአዴግ ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ነፃ መሆኑ ሳይረጋገጥና የምርጫ አፈፃፀም ችግሮች ሳይወገዱ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ለማወጅ መዘጋጀቱ ተገቢ አይደለም ሲል ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ የሚመሩት ኢማዴ-ደህአፓ ተቃወመ፡፡ መንግስት፤ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎችን ጨምሮ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ ያለው ስልጠና የምርጫ ቅስቀሳ አካል ነው ሲልም ፓርቲው ኮንኗል፡፡ የኢትዮጵያ ማህበረ ዴሞክራሲ ደቡብ ህዝቦች አንድነት ፓርቲ ሰሞኑን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባስገባው ግልፅ ደብዳቤ፤ ያለፉት አገር አቀፍና የአካባቢ ምርጫዎች ከመካሄዳቸው በፊት በምርጫ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር የሚወያይበት መድረክ እንዲዘጋጅ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም እስካሁን ከቦርዱ የተሰጠ ተግባራዊ ምላሽ የለም ብሏል፡፡ ሃገሪቱ “በአንድ አውራ ፓርቲ” ብቸኛ ቁጥጥር ስር መውደቋ አደገኛና አሳሳቢ ነው ያለው ፓርቲው፤ የመድብለ ፓርቲ ስርአት የመገንባት ተስፋችን ጨርሶ እንዳይከስም ቦርዱ ሃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የሚካሄድበትን ሁኔታ ለመፍጠር ገዥው ፓርቲና ሃቀኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚወያዩበት መድረክ እንዲያመቻች በህግ ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ የገባውን ቃል በማጠፍ መድረኩን ሳያመቻች የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀቱ ፋይዳ የለውም ብሏል - ፓርቲው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተሻሻለው የምርጫ ህግ፣ ለቦርዱ የተሰጠውን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ የማስተባበር ስልጣን ለመቀማት ታማኝ ፓርቲዎችን በተቃዋሚ ስም አሰባስቦ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ” በመፍጠር የምርጫ ውድድር አሯሯጭ አሰልፏል ሲል ፓርቲው