የሃዋሳ ስታዲዬም በ548 ሚሊዮን ብር ወጪ የግንባታ ስራው ተጀመረ
የደቡብ ክልል መንግሥት ነዋሪዎቹ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ገንዘብ እያዋጡ በመሆኑ ላለማስጨነቅ ሲል በራሱ ወጭ የአዲስ ስታዲየም ግንባታ አስጀመረ፡፡ ክልሉ ለስታዲየሙና ለተያያዥ ግንባታዎች ትናንት ሐሙስ ሚያዝያ 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ሳትኮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በ548 ሚሊዮን ብር እንዲገነባለት ውል ተፈራርሟል፡፡ ከዚህ በጀት ውስጥ 80 ሚሊዮኑን በዚህ የበጀት ዓመት ለሚሠሩ ሥራዎች የሚውል ሲሆን፣ ይህንን ጨምሮ በ2005 በጀት ዓመትም ለሥራው የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚመድበው ክልሉ ነው፡፡ ይህ የተወሰነው ሐዋሳ ከተማ ላይ ስታዲየሙን ጨምሮ የሚገነባውን ግዙፍ የስፖርት ኮምፕሌክስ እንዲያሠራ የተሰየመው ምክር ቤት ከክልሉ መንግሥት ጋር ከመከረ በኋላ መሆኑ ታውቋል፡፡ የስፖርት ኮምፕሌክስ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበርያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ አመሎ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2004 እና በ2005 በጀት ዓመት ክልሉ ከራሱ ካዝና እየመደበ ያሠራል፡፡ በ2006 በጀት ዓመት ሕዝብ ለግንባታው አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ይጠይቃል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ሥራውን ሐሙስ ተረክቦ በዕለቱ ቁፋሮ የጀመረው ሳትኮን ኮንስትራክሽን ይህንን ፕሮጀክት ለማሸነፍ ከስምንት ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ጋር ተወዳድሯል፡፡ ከስምንቱ ውስጥ ሦስቱ በቴክኒካል ጨረታ ሲወድቁ፣ አምስቱ ጨረታውን አልፈው በፋይናንስ ጨረታ ተወዳድረዋል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ ሳትኮንን ጨምሮ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን፣ ሚድሮክ ኮንስትራክሽንና ቫርኔሮ ይገኙበታል፡፡ ከአምስቱ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ውስጥ ዝቅተኛውን 548 ሚሊዮን ብር ለመጀመርያው ዙር የስታዲዮም ግንባታ በማቅረብ ሳትኮን አሸንፏል፡፡ ከፍተኛ የሆነውን የጨረታ ገንዘብ 564 ሚሊዮን ብር ያቀረበው ቫርኔሮ ሲሆን፣ ሦስቱ ኮንስትራክሽን