የቡና ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተጠየቀ
የቡናን ዘርፍን በበላይነት እንዲመራ የሚቋቋመው የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዲሆን ጥያቄ ቀረበ፡፡ ባለሥልጣኑን ለማቋቋም የተዘጋጀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ እንደሚለው ባለሥልጣኑ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር በረቂቅ ደንቡ ላይ ለመወያየት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ቡና ላኪዎች፣ ባለሥልጣኑ ለግብርና ሚኒስቴርም ሆነ ለንግድ ሚኒስቴር ተጠሪ ከሆነ ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ አደረጃጀትም ሆነ ሥልጣን አይኖረውም ብለዋል፡፡ ዘርፉ ያለበት ችግር የተወሳሰበ በመሆኑ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዲሆን ነጋዴዎቹ አሳስበዋል፡፡ አገሪቱ ትልቁን የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት የቡና ዘርፍ በተለይ ልማቱ በግብርና ሚኒስቴር፣ ግብይቱ ደግሞ በንግድ ሚኒስቴር ሆኖ ቆይቷል፡፡ የቡና ዘርፍ በእነዚህ መዋቅሮች በሚተዳደርበት ወቅት በተከታታይ ዓመታት ከቡና ዘርፍ ትልቅ ገቢ ለማግኘት ቢታቀድም፣ ጠንካራ የማስፈጸም አቅም ያለው የቡና ዘርፍ አመራር ባለመኖሩ ዕቅዱን በስኬት ማጀብ አለመቻሉ ይነገራል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ጥናቶች ከመደረጋቸውም በተጨማሪ፣ ጥናቶቹን ያካሄዱ ኤክስፐርቶች የኮሎምቢያንና የጓቲማላን ልምድ ለመቅሰም የተለያዩ ጉዞዎችን አድርገዋል፡፡ በመጨረሻ የተደረሰበት ውሳኔ በደርግ መንግሥት ዘመን ዘርፉን ሲመራ የነበረውን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መልሶ ማቋቋም ሆኗል፡፡ የቀድሞ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ በአሁኑ ወቅት ለግል ኩባንያዎች የተላለፉት በበቃ፣ ሊሙና ቴፒ እርሻ ልማት ድርጅቶችን ጨምሮ ያስተዳድር ነበር፡፡ አዲሱ ተቋም የሚያስተዳድረው እርሻ ባይኖርም፣ አገሪቱ የምታመርተውን