በቡና ላይ የተመሠረተው ህልውና
ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ ሆኗል፡፡ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ትይዩ የተገነቡት ካፌዎችና ሬስቶራንቶች በረንዳቸው በደንበኞች ተጨናንቋል፡፡ ካንዱ ካፌ ፊትለፊት ሰፋ ባለ ረከቦት የተደረደሩ ሲኒዎች ስር ሳር ተጎዝጉዞ፣ እጣን ሲጨስ ይታያል፡፡ ለቡና ቁርስም በስፌት ፈንዲሻ ቀርቧል፡፡ የዕጣኑ መዓዛ ቤቱን አውዶታል፡፡ የአገር ባህል የለበሰች ኮረዳም ቄንጠኛ በሆነ መልኩ የምትቀዳው ቡና ቀልብ ይስባል፡፡ የቡናው ሥርዓት የሚጀምረው ከረፋዱ 5፡30 አካባቢ ሲሆን፣ ስምንት ሰዓት ማብቂያው ነው፡፡ ስለዚህም የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም ደግሞ ወጣቶችና በአቅራቢያው በሚገኝ መሥሪያ ቤት የሚሠሩ ሰዎች ምሳቸውን ከበሉ በኋላ ቡና ለመጠጣት ጎራ ይላሉ፡፡ ደንበኞችም ብዙ በመሆናቸው በካፌዎቹ የሚገኙ መቀመጫዎች ሁሉ ይያዛሉ፡፡ ስለዚህም በርካታዎቹ ቆመው ለመጠጣት ይገደዳሉ፡፡ በዚህ አካባቢ ጨዋታውም ይደራል፡፡ በየካፌውና ሬስቶራንቱ በባህላዊ ሥርዓት የሚቀርበው ቡና በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ሆኗል፡፡ እናም የቡና ሰዓት ከማለፉ በፊት ለመድረስ ይጣደፋሉ፡፡ ሀብታሙ አዲሱንም ያገኘነው የቡና ደንበኛው ወደ ሆነው ካፍቴሪያ ለመሄድ ሲዘጋጅ ነበር፡፡ ምንም እንኳን በየቀኑ ቤተሰቦቹ ቡና ቢያፈሉም የዘወትር ደንበኛው ወደ ሆነው ሬስቶራንት ጎራ ብሎ ከቅርብ ጓደኛው ጋር ቡና እየተጎነጨ መጫወት ልምድ ሆኖበታል፡፡ በቡና ሰዓት በሬስቶራንቱ ውስጥ የሚኖረው ድባብም ደስ ያሰኘዋል፡፡ የቡና ሱስ ባይኖርበትም ሰዓቱን ጠብቆ የመጠጣት ልምድ አለው፡፡ ‹‹አንዳንድ ሰዎች የቡና ሥርዓቱን እያዩ ለመጠጣት ሲሉ ብቅ ይላሉ፡፡ ምናልባትም አቀራረቡ የተለየ መስህብነት ስላለው ደንበኞች መቀመጫ ቦታ ቢያጡ እንኳ ቆመው እንዲጠጡ አድርጓቸዋል፡፡ ዋጋውም ሦስት ብር ከሃምሳ ሳንቲም በመሆኑ ኪስ አይጎዳም፤›› ይላል