የኢቦላ ምልክት ለሚታይባቸው መታከሚያ የተለየ ሆስፒታል ተዘጋጀ
- ወረርሽኙ በረራ የሚያስቆምበት ደረጃ አልደረሰም ተብሏል የኢቦላ ምልክት የሚታይባቸው ሰዎች የሚታከሙበት የተለየ ሆስፒታል በአዲስ አበባ ከተማ ተዘጋጀ፡፡ በኮተቤ ገብርኤል አካባቢ የሚገኘውና 95 በመቶ ያህል የተደራጀው ሆስፒታል ለጊዜው 10 አልጋዎች ሲኖሩት በቀጣይ 50 ይደርሳሉ ተብሏል፡፡ በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተውንና ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች የገደለውን የኢቦላ ወረርሽኝ ተከትሎ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያለውን ዝግጁነት አስመልክቶ ነሐሴ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ የኢቦላ ተጠቂ ያላስመዘገበች ቢሆንም በማንኛውም ሰዓት ግን ወረርሽኙ ሊገባ ይችላል ብሏል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ እንደተናገሩት፣ የኢቦላን ምልክት የሚያሟላ ጉዳይ እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ አልገባም፡፡ ኢቦላን የሚመስል ምልክትና ከምዕራብ አፍሪካ ወደዚህ የተጓጓዘ ታካሚ ሲኖር በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲደረግ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱ ተገልጿል፡፡ ከናይጄሪያ የመጡ ሁለት ቻይናውያን በኮሪያ ሆስፒታል ተኝተው ሲታከሙ በተደረገ ምርመራ ታካሚዎቹ ወባ እንደያዛቸው ታውቋል፡፡ ሆኖም ኢቦላ በማንኛውም ጊዜ ሊገባ ይችላል ተብሎ ስለሚጠበቅ፣ ኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያጠናቀቀች መሆኑን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ከቅድመ ዝግጅቶቹ መካከል አዲስ የተለየ ጠቅላላ ሆስፒታል ማቋቋም አንዱ ሲሆን፣ ይህም ተዘጋጅቶ የጤና ባለሙያዎች እንደተመደቡለትም ተገልጿል፡፡ ወረርሽኙ ወደ ምዕራብ አፍሪካ ከሚደረጉ የአየር በረራዎች ጋር ተያይዞ የመግባት ዕድሉ ሰፊ በመሆኑ፣ ከናይጄሪያ አራት ከተሞችም ወደ ኢትዮጵያ በረራዎች ስላሉና በቀን በአማካይ 500 የሚደርሱ ተጓዦች እዚህ ስለሚደርሱ ሥጋቶች አሉ፡፡ ከዚህ ጋር