ወደ ሀዋሳ የሚገቡ የኮንትሮባንድ እቃዎች እየተበራከቱ መጥተዋል - ነዋሪዎች
አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 20 ፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) ወደ ሀዋሳ ከተማ የሚገቡ የኮንትሮባንድ እቃዎች መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ይገልፃሉ ። ነዋሪዎቹ በዋናነት ከኬንያ ተነሰተው በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ከተማዋ እየገቡ ያሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች ህጋዊ ነጋዴዎችን ከመጉዳቱም በላይ የንግድ ውድድሩ ላይ አሉታዊ ተጽህኖ እየፈጠረ እንደሚገኝም ነው የሚናገሩት። እቃዎቹን ሰውሮ የማስገባት ስልቱ በየጊዜው እየተቀያየረ መምጣቱን እና አንዳንድ የፍታሻ ጣቢያዎች ላይ የቁጥጥር ሂደቱ መላላቱን ነው ነዎሪዎች የሚጠቅሱት ። እነዚህ እቃዎች በምንም መንገድ ይግቡ እንጂ ህገወጥ በመሆናቸው መንግስት ከቀረጥ ማግኘት ያለበትን ከፍተኛ ገቢ በማሳጣት አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የንግድ ውድድሩ ላይ ሳንካ በመፍጠር ህጋዊውን ነጋዴ በማዳከም ከሚፈጥሩት ጫናም ባለፈ ፥ ተገቢውን ፍተሻ እና የጉምሩክ ሰርዓትን ተከተለው ወደ ገበያ ባለመግባታቸው በሰው ጤና እና ንብረት ላይም የከፋ ጉዳት እንደሚያደርሱም ይታወቃል። በተለይ ልባሽ ጫማና የተለያዩ ኤሌክቶሮኒክስ ውጤቶች ከሌሎቹ የበለጠውን ድርሻ የሚይዙ ሲሆን ፥ ይህ በመሆኑም ህጋዊ መንገድን ተከትለው የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ሁኔታው ነገሮችን አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው እና ጉዳዩ በአቋራጭ የመበልጸግ ስልት ተደርጎ እየተወሰደ በመሆኑም የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲወስድም ነው የጠየቁት። የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንዱስትሪ ፅህፈት ቤት ሀላፊ በነዋሪው የተነሳውን ቅሬታ በመቀበል ፥ ችግሩን ለማስወገድ በዋናነት ህገወጥ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በሀገር ላይ የሚያደርሰውን ችግር ማሳወቅ ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰዋል።