ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር!
ሰላም! ሰላም! እንዴት ናችሁልኝ? ‹‹እንደርሳለን ብለን ከመሸ ተነስተን፣ ስንገሰግስ ነጋ ምንድን ነው የሚሻለን?›› አለችላችሁ አንዷ አዝማሪ። እውነቷን ነው እኮ! ‹‹በዚህ አካሄዳችን እንኳን ልንደርስ የት እንደምንሄድም የምናውቅ አንመስልም፤›› ከእንቅልፌ እንደተነሳሁ ማንጠግቦሽን እንዲህ ብላት፣ ‹‹ኧረ ተረጋጋ። እንዴ ቅዠትና እውነትን ለይ እንጂ፤›› አለችኝ። ስንት መልካም ጅማሮዎች ባሉት በዚህ ጊዜ የእኔስ እንዲህ ማለት አይገርማችሁም? ‹‹የእኔ ባትሆኝ ይቆጨኝ ነበር፤›› አልኩ። የእውነት የእኛ አልሆን እያለን የሚያስቆጨን በዝቷል። ሌላ ምንም ሳይሆን የገዛ ኑሯችንን መውሰድ ትችላላችሁ። እኛ እየኖርነው የእኛ ይመስላል? እሱ በፈለገው እንጂ እኛ በፈቀድነው እንመራዋለን? ኧረ ጣጣ ነው ዘንድሮ ወገኖቼ! እውነቴን ነው የምላችሁ ልቤ ክፉኛ የሚዝለው እንዲህ እንዲህ ሳስብ ነው። የደላላ ልብ ጥቁር ድንጋይ ነው ያለው ማን ነው? ‹‹እኛም እኮ አንዳንዴ ሰው ነን፤›› አለች አሉ ጦጣ። ‘እኛም በቤታችን እህህ አለብን’ ሲባል ባትሰሙ ነው? ይህችን እንኳን የእኛ ሠፈር አባባል ስለሆነች ላትሰሙዋት ትችላላችሁ። አንድ ደፋር ነው አሉ፣ ‹‹ማንም ያለሙያውና ዕውቀቱ ስንት ቦታ እየገባ ነገር ሲያበላሽ እየታለፈ የእኛ ሠፈር በዚህ አባባል አትጠቆርም፤›› ብሎ የለፈፈው። ወይ የዘመኑ ፈጠራ! ሁሉንም ነገር ካዛመድነው እዚህ አገር ስለሙያና ባለሙያው ብዙ ይወራል። በየዘርፉ ለሥራቸው ባላቸው ትጋት ምሥጋና የምንቸራቸው ሰዎች ጥቂት አይደሉም እኮ። ባናስተውለው ነው እንጂ! ታዲያ በዚያው ልክ ያለ ቦታው ገብቶ የሚያደናቁረውን ስታዩ የማማረሪያ ቃላት አይበቋችሁም። በነገራችን ላይ የዘንድሮ ቃሪያ አንሰፍስፎ አላቃጥል ያለን ለምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ያለቦታቸው የገቡ የሰው ቃሪያዎች በ