ጡማኖና ፋቂሳ ስለተባሉ የሲዳማ ነገድ ኣባቶች እና መካነ መቃብሮቻቸው ምን ያህል ያውቃሉ?
ቴላሞ የጡማኖ መታሰቢያ የጡማኖ መካነ መቃብር እና የሃገር ሽማግሌው አቶ ሲዳሞ ቢረጋ ከለኩ ከተማ በስምንት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኘው ቴላሞ ነው፤ ቴላሞ የሲዳማ አድባር ነው ሲሉ የሃገር ሽማግሌዎቹ ይገልጻሉ፡፡ አረንጓዴ ምድር ምን ማለት እንደሆነ በቴላሞ ቅጥር ግቢ ያሉት ሃገር በቀል ግዙፍ የዛፍ ዝርያዎች ለትውልድ የቆሙ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ መልከአ-ምድራዊ ውበቱ ይማርካል፤ ከደኑ መሃል በአጥር የተከበበ አንድ ቅጥር አለ፤ በዚህ ቅጥር ውስጥ የሲዳማ ነገድ አባት የሆነው የጡማኖ መቃብር ይገኛል፡፡ በስፍራው በየእጽዋቱ ስር የአረብኛ ጽሁፍ ያለባቸው ድንጋዮች ይገኛሉ፤ እንደ አካባቢው ሽማግሌዎች ገለጻ እነዚህ የአረብኛ ጽሁፍ ያለባቸው ድንጋዮች መቃብሮች ናቸው፡፡ ሲዳሞ ቢራጋ የሃገር ሽማግሌ ናቸው፤ በየግዜው ለተለያየ ጉዳይ ወደ ቴላሞ ይመጣሉ፤ ይህንን ስናጠናቅር በስፍራው ያገኘናቸውም ለተመሳሳይ ዓላማ በቴላሞ ውብ ቅጥር ግቢ ለውይይት አረፍ እንዳሉ ነው፡፡ የሲዳማ የሃገር ሽማግሌዎች የሚለብሱትን ባህላዊ አለባበስ የለበሱት አቶ ሲዳሞ ቢራጋ ስፍራውን በሚመለከት አንዳንድ ጥያቄዎችን ስናቀርብላቸው በማራኪ አተራረክ ለዛ መልሰውልናል…መነሻችን ደግሞ ቴላሞ ምንድን ነው የሚል ነበር አቶ ሲዳሞ በተረጋጋ ሁኔታ ረጃጅም የቅጥሩ ዛፎች ላይ አይናቸውን ተክለው አብራሩልን…. ይሄ ቦታ ቴላሞ ይባላል፤ ጡማኖ የሲዳማ አባት ነው፤ እዚህ ነው የተቀበረው፤ ቦታው ብዙ ዓመቱ ነው….ማን ይቆጥረዋል ብዙ ነው፤ እዚህ የወለደ ሰው አሁን አስራ ስድስት ትውልድ ሆኗል፡፡ የቅጥሩን ዙሪያ ገባ በዓይናቸው ቃኘት አድርገው መልሰው ወደ ሽማግሌዎቹ በመመልከት የቴላሞን አካባቢ ሁለንተናዊ እሴት በወፍ በረር መተረኩን ቀጥለዋል….. በዓመት በዓመት ኮርማ ይገባል…