በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥቃት ተፈጸመበት
በየመን ዋና ከተማ ሰነዓ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ መጋቢት 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በጦር መሣሪያ ድብደባ ጥቃት ተፈጸመበት፡፡ ጥቃቱ በኤምባሲው ሠራተኞች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኤምባሲው ላይ ጥቃት የተፈጸመው በየትኛው ተፋላሚ ወገን መሆኑ ለጊዜው አልታወቀም፡፡ የደረሰው አደጋ ከፍተኛ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከደረሰው የጦር መሣሪያ ጥቃት በኋላም ኤምባሲው መደበኛ ሥራውን የቀጠለ መሆኑን፣ በንብረት ላይ የደረሰውን አደጋ በዕለቱ መገመት እንደሚያስቸግርና ገና ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ቃል አቀባዩ ጨምረው አስረድተዋል፡፡ በየመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሐሰን አብደላና የሥራ ባልደረቦቻቸው ከኢትዮጵያውያን በፊት የመንን ለቀው ባለመውጣታቸውና ወገኖቻቸውን ለመርዳት ሲሉ እዚያ በመቆየታቸው፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ምሥጋና አቅርበውላቸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኤምባሲው ከመንግሥት ጋር በመሆን በየመን በተቀሰቀሰው ውጊያ ምክንያት የታገቱ ኢትዮጵያውያንን የማውጣት ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ አቶ ተወልደ ጠቁመዋል፡፡ ከቀናት በፊት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየመን የሚገኙ ከ2,000 በላይ ኢትዮጵያውያንን በመመዝገብ ወደ አገራቸው በሰላም እንዲመለሱ አንድ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን ገልጿል፡፡ ከውጭ ጉይ ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሠረት እስከ መጋቢት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ 11 ሕፃናትና 12 ሴቶችን ጨምሮ 30 ኢትዮጵያውያንን ወደ ጂቡቲ እንዲጓዙ ተደርጓል፡፡ ነገር ግን በየመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በመሆኑና ከአካባቢው አስቸጋሪነት አ