ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫ ቦርድ ላይ የሚቀርቡትን የገለልተኝነት ትችቶች አጣጣሉ
‹‹ምርጫ ቦርድ እየተሰደበ የሚቀጥል አይመስለኝም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ‹‹አሁንም እደግመዋለሁ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም›› አቶ ግርማ ሰይፉ የ2007 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ ሪፖርት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችን ጠንከር ብለው በማጣጣል ተከላከሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ 18 ገጽ ባለው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸው ውስጥ ዘንድሮ አገሪቱ ከምታስተናግዳቸው ትልልቅ ኩነቶችና የቀጣይ አምስት ዓመት የአገሪቱ ጉዞን ከሚወስኑ ጉዳዮች ዋነኛው፣ በግንቦት ወር የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በግንቦት ወር የሚካሄደው አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና በሕዝቦች ዘንድ ዓመኔታ ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥት በሁሉም መስክ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረገና በቀጣይ ሒደቱን በንቃት በመከታተል መንግሥታዊ ግዴታውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብና አገላለጽ ግን ሊበተን የዚህን ዓመት መገባደድ በሚጠብቀው ፓርላማ ውስጥ የተቃዋሚው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ብቸኛ ተወካይ ለሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ አልተዋጠላቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ምርጫ ቦርድ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ላይ የሰጠው ውሳኔ፣ አቶ ግርማ የሚመሩትን የፓርቲው ወገን ዕውቅና የነፈገ በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ዛሬ እንደ ወትሮው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ዝርዝር ጉዳዮች እያነሳሁ ማብራሪያ እንዲሰጡኝ እንደማልጠይቅ የሚያውቁ ይመስለኛል፤›› በማለት የጀመሩት አቶ ግርማ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ምርጫው በሕዝብ ዘ