ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› መጠን ዛሬ ይፋ ይሆናል
የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚያቀርበው ‹‹የሶቨሪን ቦንድ›› መጠን ዛሬ ይፋ እንደሚሆን ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አመለከተ፡፡ የኢትዮጵያ ‹‹ሶቨሪን ቦንድ››ን ለመሸጥ ከተመረጡ ኩባንያዎች ጋር መግለጫው በአውሮፓ እንደሚሰጥም የገንዘብና ኢካኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሽዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ የሚመራ የኢትዮጵያ ቡድን ወደ አውሮፓ ማቅናቱን የገለጹት አቶ አህመድ፣ የኢትዮጵያን ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ለመሸጥ ከተመረጡት አመቻች ኩባንያዎች ጋር በመሆን፣ በሚሰጠው መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ በዶላር የምትሸጠው የዕዳ መጠን ወይም ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮም የዕዳ መጠኑን ወይም ቦንዱን ከሚገዙ ኢንቨስተሮች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡ ለዓለም አቀፍ ገበያው የሚቀርበው ቦንድ መጠንን ግን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሽዴ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ማለት ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ለኢትዮጵያውያን እንደቀረበላቸው ዓይነት የመንግሥት ሰነድ ሆኖ፣ ይኼኛው የሚለየው ለዓለም አቀፍ ገበያ ወይም ኢንቨስተሮች በዶላር ወይም በውጭ ምንዛሪ እንዲገዙት የሚቀርብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ከውጭ የምታገኛቸው ብድሮች በረዥም ጊዜ የሚከፈሉና በአገሮች የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት ቀላል ወለድና ረዥም የዕፎይታ ጊዜን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ግን በንግድ ወለድ መሠረት የሚገዛ ሲሆን፣ ገዢዎች ወደዚሁ ውሳኔ ከመግባታቸው በፊት የአገሪቱን ወይም የቦንዱ ባለቤት አገርን ብድር የመሸከምና አጠቃላይ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያው ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባሉ፡፡ የአንድ አገርን ወይም ድንበር ዘለል ኩባንያን ዕዳ የመ