የዝቅተኛ ደመወዝ ወሰንየለሹ ኢኮኖሚ
ያሰረችው የወየበ ሻሽ ሙሉ በሙሉ ፀጉሯን አልሸፈነላትም፡፡ አቧራ የጠጣው ፀጉሯ በዚህም በዚያም አፈትልኮ ይታያል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 አቅራቢያ ከሚገኝ የግንባታ ሳይት ላይ ያገኘናት አብነት ነጋሽ፣ ፀሐይ የጠበሰው ፊቷ ስለ ሥራዋ ፈታኝነት ብዙ ይናገራል፡፡ ምንም እንኳ ወቅቱ ሙቀት ቢሆንም አብነት በልብስ ላይ ልብስ ደራርባለች፡፡ ሱሪ፣ በሱሪ ላይ ቀሚስ፣ ሹራብ፣ አንገቷ ላይ ሻርፕ አድርጋለች፡፡ በካልሲ የተጫማችው አሮጌ ኮንጐ እንደዚያ መውጣት መውረድ ባለበትና ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚጠይቅ የሥራ አካባቢ ምቾት የሚሰጥ አይመስልም፡፡ ምንም እንኳ ከታች እስከ ላይ እንደዚያ መልበሷ ከሥራው ጋር እንዲሄድ በማሰብ ቢሆንም፡፡ ሸዋ ምንጃር አካባቢ የተወለደችው የ33 ዓመቷ አብነት የምትኖረው ገርጂ አካባቢ ሲሆን ከሥራ ቦታዋ የምትገኘው ማልዳ በመነሳት በእግሯ ተጉዛ ነው፡፡ መንገዱ አንድ ሰዓት የሚወስድባት ሲሆን ዘወትር ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ ከሥራ ገበታዋ ትገኛለች፡፡ ትራንስፖርት፣ ቁርስና አለባበስ የሚባሉ ነገሮች ለሷ ብዙ ትርጉም የሚሰጡ ነገሮች አይደሉም፡፡ ስትመለስም በተመሳሳይ መልኩ በእግሯ እያዘገመች ነው፡፡ ረዥም ሰዓት መሥራት፣ በቀላሉ ንፁህ ውኃ ማግኘት አለመቻል፣ በተወሰነ መልኩ እንኳ ተመቻችተው ልብስ የሚቀይሩበት ወይም የሚመገቡበት ቦታ አለመኖር የየዕለቱ የሥራ ላይ ፈተናዎቿ ናቸው፡፡ በቀን የሚከፈላት 35 ብር ነው፡፡ ‹‹ቀን በቀን ሁሉም ነገር እየጨመረ የሚከፈለው ምንም ማለት አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ካልሠራን ምን እንበላለን፤›› ትላለች፡፡ ወርቅነህ ፈለቀ የመንገድ ሥራ ላይ በተሰማራ አንድ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የፌራዮ ሠራተኛ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ ድርጅቱ በመንገድ ሥራው ላይ ከተሰማራ ከሞላ ጐደል ሁለት