የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት መመሥረቻ ሰነዶች ላይ ስምምነት ተደረሰ
ከመስከረም 29 እስከ መስከረም 30 ቀን 2007 ዓ.ም. በመተዳደሪያ ደንቡና በሥነ ምግባር ደንቡ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገው የመጨረሻ የምክክር መድረክ ላይ በተፈጠረው ስምምነት ምክንያት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በምሥረታ ዋዜማ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ መሥራች ጉባዔው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡ በሁለቱ ቀናት ውይይት ጋዜጠኞች፣ የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች፣ የጋዜጠኝነት ትምህርት የሚሰጡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች፣ የሚዲያ ተመራማሪዎችና አማካሪዎች፣ የመንግሥት ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የአፍሪካ አዳራሽ ስለመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ለሁለት ቀናት በተደረገው ውይይት ባለፉት አሥር ዓመታት ሲያወዛግቡ የነበሩ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ በመድረሱ፣ ‹‹ትልቅ ዕርምጃ›› እንደሆነ የምክር ቤቱ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡ ምክር ቤቱን ለመመሥረት ቁልፍ የሆኑት የመተዳደሪያና የሥነ ምግባር ደንቦች ላይ ሰፊና በንቁ ተሳትፎ የታጀበ ግልጽ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በተለይ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ታቅፈው ያሉ አንዳንድ ነጥቦች አወዛጋቢነታቸው ግልጽ ነበር፡፡ በመተዳደሪያ ደንቡ የተካተቱት የሕግ መሠረት፣ የተፈጻሚነት ወሰን፣ ሕጋዊ ሰውነት ለመስጠት የሕግ ሥልጣን ያለው የመንግሥት አካልን መለየት፣ በምክር ቤቱ አባልነት መሠረት ግለሰብ ጋዜጠኞች ሳይሆኑ የሚዲያ ተቋማት መሆናቸው፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላት የአገልግሎት ዘመን አራት ዓመት መሆን፣ የፓናል አባላት ስብጥርና ምንጭ፣ የመንግሥት ሚናና የምክር ቤቱ የገቢ ምንጭ ዘርፈ ብዙና ሰፋ ያለ የውይይት መነሻ ነበሩ፡፡ ከመተዳደሪያ ደ