የዓለም ባንክ ኢትዮጵያ ለብድር ዕዳ አደጋዎች የመጋለጥ ዕድሏ እየሰፋ ነው አለ
ሰሞኑን ለሦስት ቀናት ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የኦፕሬሽን ዋና ኃላፊ ስሪ ሙሊያኒ ኢንድራዋቲ፣ እያደገ የመጣው የብድር ዕዳ መጠን በኢትዮጵያ ላይ አደጋዎችን ሊያስከትል እንደሚችል ገለጹ፡፡ ኢንድራዋቲ ባለፈው ረቡዕ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ ምንም እንኳን የአገሪቱ የብድር ዕዳ መጠን ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ አነስተኛ ቢሆንም፣ የዕዳውን መጠን በግልጽነት ለማስተዳደር የሚችልና ግልጽነት የሰፈነበት አስተዳደር ማስፈን የመንግሥት ግዴታ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አገሪቱ ያለባት ጠቅላላ የብድር መጠን 20 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 12 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ምንጮች የተገኙ ብድሮችን የሚሸፍን የዕዳ መጠን ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከጠቅላላ አገር ውስጥ ምርት አኳያ የዕዳው ድርሻ 44 ከመቶ መድረሱን ይጠቁማል፡፡ ኢንድራዋቲ እንደሚገልጹት፣ ይህ አኃዝ ዝቅተኛ በሚባለው የዕዳ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ነገር ግን የመንግሥት የኢንቨስትመንት ወጪዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ምክንያት የዕዳ መጠኑን በዚያው ልክ እያደገ በመሆኑ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በሚመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከሚመለከታቸው ሚኒስትሮች ጋር መነጋገራቸውን አስረድተዋል፡፡ ከውይይቶቹ መካከልም በመንግሥት አስተዳደር ማሻሻያ ሪፎርሞች ላይ ያተኮረው አንዱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚህም መንግሥት በአስተዳደራዊ መዋቅሮቹ ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ ግልጽነትና ኢኮኖሚውን በብቃት የማስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የኢንቨስትመን