በአገራችን ያልቀረው ሕፃናትን የመቅጣት ‹‹መብት››
በቤተሰብና በትምህርት ተቋማት አካባቢ የሕፃናትን ጠባይ ለማረም የሚወስዱ የቅጣት ዕርምጃዎች በየወቅቱ አነጋጋሪ ናቸው፡፡ አንዳንዶች ሕፃናት ካልተቀጡ፣ ካልታረሙ፣ ካልተገሰጹ ጥሩ ሥነ ምግባር አይኖራቸውም፤ ባህላችንም፣ ሃይማኖታችንም ሕፃናት እንዲቀጡና መልካም ጠባይ ኖሮአቸው እንዲያድጉ ያስተምራሉ የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡ ይህንን አቋም የማይቀበሉት ሌሎቹ ደግሞ ሕፃናትን በማስተማር፣ በመንገር፣ በትዕግስት ቀርቦ በማስረዳት ካልሆነ መቅጣት አያስተምራቸውም፣ አያርማቸውም፤ እንዲያውም የሥነ ልቦና ጫና በማሳደር እንዲፈሩ፣ እንዲጨነቁና ሐሳባቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ ያደርጋል በሚል የተቃውሞ ክርክራቸውን ያሰማሉ፡፡ ከተወሰኑ ዘመናት በኋላ ደግሞ ሕፃናትን ጠባይ ለማረምም ቢሆን መቅጣት የሰብዓዊ መብት ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ያም ሆኖ ሕፃናትን መቅጣት አሁንም በብዙ አገሮች ሕጋዊ የሆነ ተግባር ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል፡፡ ከሕፃናት መብት አንፃር አገራችን በዚህ ዘመን ከትናንቱ የተሻለ ቢሆንም ሕፃናት መቀጣታቸው፣ መቆንጠጣቸው፣ በእጅ ወይም በዱላ መመታታቸው የቀረ አይመስልም፡፡ በቀደሙት ዘመናት በቤት ውስጥ ያጠፋ ሕፃንን መግረፍ፣ በበርበሬ ማጠን፣ ቀዝቃዛ ውኃ ውስጥ መንከር፤ በትምህርት ቤትም ለረጅም ሰዓታት እንዲንበረከክ ማድረግ፣ በክፍል አለቃና በመምህር በትር መገረፍ፣ አጎንብሶና ተገልብጦ ጆሮን መያዝ የተለመዱ እንደነበሩ ብዙኃኑ የኅብረተሰብ ክፍል የሚያስታውሰው ሃቅ ነበር፡፡ አሁን ለውጡ አገራችን ከሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጋር ባመጣችው የባህል ለውጥ ይሁን በዘመናዊነት ወይም በዘመነ ሉላዊነት (Globalization) ተፅዕኖ ሕፃናት እንደ ድሮው ዓይነት ለከፋ ቅጣቶች አይጋለጡም፡፡ አሁንም ቢሆን ግን መቀጣት፣ መገረፍና መቆንጠጥ አልቀረላቸውም፡