የቡና ምርትና ግብይት የሚቆጣጠር መንግሥታዊ ተቋም ሊቋቋም ነው
- አዲስ የቡና ስትራቴጂ እየተቀረፀ ነው ቡናን ከምርት ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለውን የግብይት ሒደት የሚቆጣጠር፣ በቡና ላይ የሚሠሩ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶችን በአንድ ላይ ጠቅልሎ የሚሠራ አዲስ መንግሥታዊ ተቋም ሊቋቋም ነው፡፡ ከቡና ምርትና ግብይት ሒደት ጋር ተያይዞ አለ የሚባለውን ችግር ለመቅረፍ ያስችላል የተባለውን አዲሱን መንግሥታዊ ተቋም ለመፍጠር የሚያስችለው ጥናት ተጠናቅቆ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀርቧል፡፡ የተቋሙ አስፈላጊነት ላይ ውሳኔ ከደረሰ በኋላ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በቡና ምርትና ግብይት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ቡናን የሚቆጣጠር መንግሥታዊ ተቋም እንዲቋቋም መወሰኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ እንደ ምንጮች ከሆነ እስከዛሬ የነበረውን የቡና ግብይት ሙሉ ለሙሉ የሚለውጥና አዲስ አሠራርን ይፈጥራል የተባለው ይህ ተቋም በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሥራ ይገባል፡፡ ተቋሙን ለመፍጠር የተደረገው ጥናት ተጠናቆ ለመንግሥት ከመቅረቡ በፊት የሌሎች የቡና አምራች አገሮች ልምድ እንዲወሰድ መደረጉም ተገልጿል፡፡ በተለይ በቡና ላይ የሚታየውን ረዥም የግብይት ሰንሰለት በመስበር ቀልጣፋ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር በማድረግ በአገር ውስጥ የቡና ዋጋ እንዳያሻቅብ ለማድረግ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድንም ለመቆጣጠር የሚያስችል አሠራር የሚኖረው ሲሆን፣ የቡና ምርታማነትም እንዲያድግ የሚያስችል አሠራር እንደሚከተልም ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ ተቋም መቋቋም ጎን ለጎን አዲስ የቡና ስትራቴጂ በመዘጋጀት ላይ ነው፡፡ ስትራቴጂው በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ኢትዮጵያ ከብራዚል ቀጥላ ሁለተኛዋ የ