የእኛ አገር ትምህርት ሁለት የቆዩ የቁልፍ ችግሮች
(በተለይ በመለስተኛና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ) በሳምራዊት ኅሩይ የኢትዮጵያ ትምህርት ከፍተኛ የውድቀት ታሪክ በእጅጉ ከደርግ ዘመን ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ትርምስ፣ ርዕዮተ ዓለማዊና ፕሮፓጋንዳዊ እመቃ፣ የዘመቻና የጦርነት ጣጣዎች ኅብረተሰቡንና ትምህርቱን አዳሽቀውታል፡፡ በየትም ቦታ ቅድሚያ ይሰጠው የነበረው የፓርቲ፣ የፖለቲካ፣ የፕሮፓጋንዳ፣ የክብረ በዓልና የዘመቻ ሥራ ነበር፡፡ የሚያስመሰግነው፣ የሚያሸልመውና የሚያሾመው ይህ ዓይነቱ ‘አብዮታዊ ሥራ’ ነበር፡፡ ከትምህርቱ አስተዳደር አንስቶ እስከ መምህራን ድረስ በ‹‹አብዮታዊ ግዴታዎች›› መጠመድና ሥራ መፍታት እየበዛ ትምህርቱ ተዝረከረከ፡፡ ሥራ ትጋትና ዋጋ አጥቶ፣ ሥራ ጠሉ ሁሉ ‹‹አብዮታዊ›› እና ‹‹ጓድ›› እየተባለ ጥቅማ ጥቅሙን ሲቀራመትና የታታሪው ገምጋሚና አዛዥ ሲሆን የሥራ ፍቅርና ትጋት ሞተ፡፡ ‹‹አብዮታዊ አስተዋጽኦ››፣ ‹‹ጓድ››ነትና የ‹‹ጓድ›› ዘመድነት ከትምህርት ቤት የማያባርር፣ ልዩ ፈተና የሚያሰጥ፣ ፈተና የሚያሳልፍ፣ ከደንብ ውጪ ለመድገምና ማትሪክን ደጋግሞ በመደበኛነት ለመፈተን የሚያስችል እየሆነ በመምጣቱ የሙያ ሥነ ምግባሩ ተቦዳደሰ፡፡ የመምህራን ከሥራ መጓደል የተማሪን ታጉሮ መዋል እያስከተለ፣ የመምህራን የሥራ ስሜትና ሥነ ምግባር መውደቅ የተማሪውን ችሎታ እያደከመ፣ 12ኛ ክፍል ደርሶ የማለፍ ዕድልም ህልም እየሆነ መሄድ ራሱ ተስፋ እያሳጣ የተማሪው የትምህርት ስሜትና ትጋት ይጠፋል፡፡ የወጣት አጥፊነት ይለማል፡፡ የትምህርቱ መፋለስና የይስሙላ መሆን የግምግማና የማለፊያ ሥርዓቱን ያፋልሰዋል፡፡ በአግባቡ ያላስተማረ መምህር በቀላል ፈተና፣ ብዙ ተማሪ ከወደቀም ነጥብ በመጨመር ጉድ መሸፈን ውስጥ ይገባል፡፡ ያልሠራና ተስፋ ያጣ ተማሪም በበኩሉ በኩረጃ፣ በዛቻ