መድረክ ሕይወታቸው ላለፈና ንብረታቸው ለወደመባቸው ዜጎች መንግሥት ካሳ እንዲከፍል ጠየቀ
ምንጭ፦ www.ethiopianreporter.com የአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን ተጠቃሚ የሚያደርገውን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላን መሠራትን አስመልክቶ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ባደረጉት ሰላማዊ ሠልፍ ላይ በተፈጠረ ግጭት ሕይወታቸው ላለፈ ቤተሰቦችና ንብረታቸው ለወደመባቸው ባለሀብቶች፣ መንግሥት ካሳ መክፈል እንዳለበት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ጠየቀ፡፡ መድረክ ‹‹ለሰላማዊ ተቃውሞ ጥይት ምላሽ ሊሆን አይገባም›› በሚል መሪ ቃል ግንቦት 16 ቀን 2006 ዓ.ም. መነሻውን ከግንፍሌ ወንዝ ድልድይ አድርጐ በቤልኤር ሆቴል፣ በህንድ ኤምባሲ፣ በአዋሬ አደባባይና በአድዋ ድልድይ በማድረግ በድንበሯ እናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል ጀርባ በሚገኘው የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ሜዳ ላይ ባጠናቀቀው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ፣ ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሐሳቦችን አቅርቧል፡፡ የመድረክ አባልና የፓርላማ ተመራጭ የነበሩት አቶ ገብሩ ገብረ ማርያም መድረክ ለምን ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ እንደተገደደ ሲናገሩ፣ ‹‹ኢሕአዴግ ራሱ ላወጣው ሕገ መንግሥት ባለመገዛት ኢሕገ መንግሥታዊነቱን አረጋግጧል፡፡ ትግላችን ኢዲሞክራሲያዊ ሒደቶች እንዲታረሙ ነው፡፡ በአገሪቱ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተው ችግር የዲሞክራሲና የሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር እጦት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲጣስ ‹‹መብቴ ተጥሷል›› ማለት ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን የገለጹት አቶ ገብሩ፣ የአዲስ አበባንና የልዩ ዞኖቹን የጋራ ልማት ትስስር ሽፋን፣ ሕዝብ ያልተወያየበትንና ያልተስማማበትን ለመተግበር መነሳት ኢሕገ መንግሥታዊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሕዝቡና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያነሱ