በሐዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ከመልካም ተሞክሮ ባሻገር ጥቃቅን ችግሮችም አይናቁ
ወደ ሐዋሳ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ግቢ ስዘልቅ ሞቃታማ አየሯን የምትረጨውን ፀሐይ ተቋቁመው በየትምህርት መስካቸው ተግባራዊ ልምምድ የሚያደርጉ ተማሪዎች እዚህም እዚያም ሲታትሩ ታይተውኛል። በስተቀኝ በመንገድ ሥራ የሚሠለጥኑ ተማሪዎች አፈሩን እየደለደሉና እየጠቀጠቁ ጥራት ያለው መንገድ እንዴት መሥራት እንደሚቻል ተግባራዊ ልምምድ ሲያደርጉ፤ በስተግራ ደግሞ በኮብል ስቶን ሥራ እና በቅየሳ የሚሠለጥኑ ተማሪዎች በየሙያቸው የሚያስፈልጓቸውን ቁሶች ታጥቀው ሙሉ ትኩረታቸውን በልምምዱ ላይ አድርገው ይታያሉ። ከተማሪዎቹ መካከል ወደ አንዱ ጠጋ ብዬ « ሥልጠና እንዴት ነው ?» የሚለውን የጋዜጠኛ ጥያቄዬን አስቀደምኩ። ተማሪው አራርሶ ወልዴ ይባላል። የመጣው ከሀዲያ ዞን ሾኔ ከሚባል አካባቢ ነው። የሦስተኛ ዓመት የመንገድ ሲቪል ዎርከ ሠልጣኝ ሲሆን፤ በኮሌጁ በነበረው ቆይታ በክፍተትና በመልካም ተሞክሮነት የሚጠቀሱ ጉዳዮችን እንዲህ በማለት ይገልጽልኝ ጀመር « ባለፉት ዓመታት የመምህራን እጥረት ነበር። በሳምንት አምስት ቀን መማር ቢኖርብንም አንዳንድ ቀን መምህራን እየጠፉ ትምህርት የማናገኝበት ቀን ነበር። ይሁን እንጂ ያሉት መምህራን ጊዜያቸውን በመሰዋት ትምህርት እየሰጡን ክፍተቱን ለመሙላት ይጥሩ ነበር። አንዳንድ ለተማሪ ፍቅር የማይሰጡ መምህራንም ነበሩ። ተማሪ ሊያጠፋ ይችላል መምህር መቻል፣ መምከርና ትምህርቱን በአግባቡ መስጠት መቻል አለበት። » ሠልጣኝ አራርሶ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ሰባ ከመቶ ተግባር ተኮር እንዲሆኑ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የሚሰጠው ሥልጠና በኮሌጃቸው በአግባቡ እየተተገበረ መሆኑን ይናገራል። ሰላሳ በመቶ የሚሆነውን ሥልጠና በክፍል ከተማሩ በኋላ ቀሪውን በተግባር ይሰለጥናሉ። በእነርሱ የሥልጠና ዘርፍ የተሟሉ የተግባር ት