በልማትና በወረራ መካከል የሚዋልለው የእርሻ መሬትና የአርሶ አደሩ እንባ
በቶፊቅ ተማም የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አንድ አካል በማድረግ የጀመረው ሰፋፊና ለም የእርሻ መሬቶችን ለውጭ አገር ባለሀብቶች በስፋት መስጠት መጀመሩ, ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተቃውሞ ካስነሱበት የኢኮኖሚ ዕርምጃዎች አንደኛው ሆኖ በመዝለቅ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ተቃውሞው ከተለያዩ አካላት እንደቀጠለ ቢገኝም፣ በመንግሥት በኩል ያሉ ቅሬታዎችን ከመፍታት ይልቅ የሚነሱት ችግሮች በአብዛኛው መሠረት ቢስ ናቸው ሲል እየሞገተ ነው፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ልዩነት ርቀት በጣም እየሰፋ ከመጣ የቆየ ሲሆን፣ መንግሥት ትችቶችን በተለመለከተ በሚያቀርበው ምክንያት በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ልማት የማያስደሰታቸው አካላት ትችት ነው ሲል ቢያጣጥልም፣ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መምጣታቸውን ቀጥለዋል፡፡ መንግሥት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን በውጭ ባለሀብቶች እንዲለሙ የማድረጉ አቅጠጫ ዋነኛ ዓላማ አገሪቱ ካላት 112 ሚሊዮን ሔክታር ውስጥ ከ 60 እስከ 70 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው ተስማሚ የሆነ ቴክኖሎጂና አመራር ቢያገኝ ሊለማ የሚችል መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካትና ሰፊ መሠረተ ልማትና ሰፊ የሆነ ካፒታል የሚጠይቅ በመሆኑ፣ እነዚህን ሰፋፊ መሬቶች ለማልማት የሚያስችል ካፒታል፣ ዕውቀትና ከፍተኛ አቅም ላላቸው ባለሀብቶች የአገሪቱን ድንግል መሬት (Prime Soil) በቅናሽ ዋጋ በሊዝ በማከራየት ለባለሀብቶች ቢሰጥም፣ የባለሀብቶቹ ኢንቨስትመንት የታሰበውን ያህል ውጤታማ ሊሆን አልቻለም፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ወስደው ወደ ሥራ ከገቡት መካከል ብዙ የተባለላቸው የቻይና፣ የህንድና የሳዑዲ ኩባንያዎች ያስመዘገቡት ውጤት አናሳ መሆኑ ሲሆን፣ ለዚህም ካሩቱሪ