ማህበራትና ዩኒየኖች በምርት ገበያው እንዴት መሳተፍ ይችላሉ?
የፌደራል የኀብረት ሥራ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚጠቁመው በአገራችን እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ድረስ 26 ሺ 672 የኀብረት ሥራ ማህበራት አሉ፡፡ እነዚህ ማህበራትም በድምሩ ከ 5 ነጥብ 89 ሚሊዮን በላይ አባላት እንዳሏቸው መረጃው ይጠቁማል፡፡ ይህም ማለት ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ህዝብ 13 በመቶ ገደማ ያህሉ ቢያንስ የአንድ ማህበር አባል ሆኗል ማለት ሲሆን፣ በጾታ ተዋፅኦ ሲታይም 85 በመቶ ወንዶችና 15 በመቶ ሴቶች በእነዚህ ማህበራት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በድምሩ 1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ያላቸው የኀብረት ሥራ ማህበራቱ ከ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አባላትና ሌሎች ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኀብረት ሥራ ማህበራቱ ተደራጅተው 177 ያህል ዩኒየኖችን መሥርተዋል፤ ዩኒየኖቹ በበኩላቸው የአባል ማህበሮቻቸውን ጥቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ የተደራጁ ሥራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በግብርና ግብይት ዘርፍ ዩኒየኖች እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አገራዊ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከዛሬ አምስት ዓመት ወዲህ የግብርና ኀብረት ሥራ ዩኒየኖች ማዳበሪያ ከውጭ በማስመጣት ተግባር ላይ ተሠማርተው የአገሪቱን የማዳበሪያ ፍላጐት 70 በመቶ ያህል የሚሸፍን ግብይት ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከሞላ ጐደል የአገሪቱ የማዳበሪያ ፍጆታ ሙሉ በሙሉ በማህበራትና ዩኒየኖች አማካይነት ከውጭ እየተገዛ በመቅረብ ላይ ነው፡፡ በቡና ምርትና ግብይት ዘርፍም እንዲሁ ጠንካራ የቡና ገበሬዎች የኀብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች ተመሥርተው የአባሎቻቸውን ጥቅም የሚያሳድጉ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላቸው ድርሻም ቀላል በማይባል ደረጃ ዕድገት እያ