የኢኮኖሚ ዕድገቱ ባለ አንድ አሃዝ ሆኖ እንደሚቀጥል የተመድ ሪፖርት ይፋ አደረገ
ሪፖርተር ያቀናበረው ይህ የሥዕል መግለጫ፣ የላይኛው መስመር በያመቱ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚወክል ሲሆን የታችኛው መስመር ደግሞ ዓመቱን እ.ኤ.አ. ይጠቁማል) - የዋጋ ግሽበት እያንሰራራ ወደ ሁለት አሃዝ ማምራቱ ይጠበቃል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከጥቂት ቀናት በፊት ይፋ ያደረገው፣ የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታና መጪውን ጊዜ የተነበየበት የዘንደሮው ሪፖርት፣ (World Economic Growth Situation and Prospects) የዓለምን ኢኮኖሚ ዕድገት በየቀጣናው ተንትኗል፡፡ በዚህ ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ ምንም እንኳ የኢኮኖሚዋ ዕድገት ትልልቅ ከሚባለው ጎራ ቢሰለፍም፣ በመንግሥት የታቀደውን መጠን ሆኖ አልተገኘም፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በአንድ አሃዝ ተወስኖ፣ ከስድስት ዓመት በፊት ከነበረበት የ12 ከመቶ ዕድገት በግማሽ ያህል እየወረደ መምጠቱንና በዚሁ መጠን እንደሚቀጥልም ትንበያው ይጠቁማል፡፡ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከ6.4 ከመቶ ያልበለጠ ዕድገት እንደሚኖርም ይጠበቃል፡፡ በአንጻሩ የዋጋ ግሽበትም (ምርትና አገልግሎቶች በአጠቃላይ የሚያሳዩት የዋጋ ጭማሪ) እያንሠራራ እንደሚቀጥልና ወደ ሁለት አሃዝ እንደሚጠጋ ተመድ ይፋ አድርጓል፡፡ መንግሥት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት የሚጠብቀው የአገሪቱ ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ- ጂዲፒ) በዝቅተኛው ዕርከን 11 ከመቶ፣ በከፍተኛው የዕድገት ጣሪያ ደግሞ 14 ከመቶን እየረገጠ እንደሚጓዝ ነበር፡፡ ሆኖም ከመንግሥት በወጣው መረጃ እንኳ ከታየ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከታሰበው በታች በስምንት ከመቶ ክልል ውስጥ እያደገ ይገኛል፡፡ ካስቀመጠው ውጥን በታች ዕድገቱ መጓዙ ያሳሰበው መንግሥት፣ በተለያዩ ጊዜያት ባስተላለፋቸው መግለጫዎቹም ካሰበ