ግብፅ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ ብድርና ዕርዳታ እንዳይሰጡ እየተንቀሳቀሰች ነው ተባለ
‹‹ለሱዳን የተሰጠ መሬት የለም›› መንግሥት ዓለም አቀፍ አበዳሪና ለጋሽ ድርጅቶች ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን ብድርና ዕርዳታ እንዲያቆሙ ግብፅ እየተንቀሳቀሰች መሆኗን መንግሥት መረጃ እንዳለው አስታወቀ፡፡ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር ሦስተኛ ስብሰባ በቅርቡ ያለውጤት ከተበተነ በኋላ፣ በግብፅ በኩል አፍራሽ የሆኑ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓርብ ረፋድ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ዲና፣ በግብፅ በኩል የቀረበውና በኢትዮጵያና በሱዳን ውድቅ የሆነው ሐሳብ፣ እስካሁን ግድቡን አስመልክቶ የተጀመሩ ውይይቶችን ወደኋላ የሚመልስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የውጭ ባለሙያዎች ያሉበትና ከሦስቱም አገሮች የተውጣጡ የውኃ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የኤክስፐርቶች ፓነል ለአንድ ዓመት በግድቡ ዙሪያ ጥናት አካሂዶ ባወጡት ሪፖርት፣ ከተወሰኑ ቴክኒካዊ ማስተካከያዎች ውጪ ግድቡ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላ መሆኑን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የፓነሉ ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ የሚያደርግ ከሦስቱ አገሮች የተውጣጡ የውኃ ባለሙያዎች ያሉበት ኮሚቴ የተቋቋመ መሆኑን፣ ግብፆች አዲስ የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የኮሚቴውን ሥራ በበላይነት እንዲከታተል የሚል ሐሳብ ነው ያቀረቡት፡፡ እንደ አምባሳደር ዲና ገለጻ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ፓነል መቋቋም ላይ ሳይሆን፣ ሚናውን በተመለከተ ነው፡፡ በዚህ ልዩነት የተነሳ ያለውጤት ስብሰባው ከተበተነ በኋላ፣ ግብፆች በሚዲያዎቻቸው ‹‹ኢትዮጵያ ለመተባበር እምቢተኛ ሆነች›› እያሉ እያቀረቡ መሆኑንና ከዓለም ባንክ፣ ከአይኤምኤፍና በሌሎች ዓለም አቀፍ