የሐዋሳ ሐይቅን «ደህንነት ለመጠበቅ ተኝተን አናድርም» - የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ዮናስ ዮሴፍ
የሐዋሳ ሐይቅን ከብክነት ለመከላከል የከተማው ነዋሪም ሆነ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የተሠማሩ አካላት ሚናቸውን ማጐልበት ይጠበቅባቸዋል፤ ለመጥለቅ የዳዳችው ጀምበር ሙሉ ለሙሉ ከእይታ ከመሰወሯ በፊት ከአድማሱ ጥግ ሆና የፈነጠቀችው ነፀብራቅ የሐይቁን ውበት አጉልቶታል። አእዋፍ ከእንቅስቃሴያቸው እየተገቱ በሐይቁ አካባቢ በሚገኙ ትልልቅ ዛፎች ላይ መቀመጥ ጀምረዋል፤ ድምፃቸውም ብዙም አይሰማም። በነፋሱ ኃይል በሚገፋው የሐይቁ ውሃ ላይ ሆነው ጥቂት አዕዋፋት ወዲያ ወዲህ ይላሉ። በሐይቁ እምብርት ላይ በርቀት ሲታዩ የነበሩት ጀልባዎችም ወደ ሐይቁ ዳር እየተፋጠኑ ናቸው። ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አዛውንቶች በሐይቁ ዙሪያ ታድመዋል። የዲላ ከተማ ነዋሪው አቶ ሳሙኤል ንጉሴ በንግድ ሥራቸው ምክንያት ወደ ሃዋሳ ከተማ ይመላለሳሉ። ቢያንስ በወር አንዴ ብቅ እንደሚሉም ነው የሚናገሩት። « ፍቅር የሆነውን የሃዋሳ ሐይቅ ሳልጎበኝ በጭራሽ አልመለስም » ይላሉ። ወሩን ሙሉ በሥራቸው ምክንያት የተፈጠረባቸውን ጫና በሐይቁ በሚያደርጉት የደቂቃዎች ቆይታ እርግፍ አድርገው አስወግደው በአዲስ መንፈስ እንደሚመለሱም ነው የሚናገሩት። ወይዘሮ ማርታ አክሊሉም ልክ እንደ አቶ ሳሙኤል ወደ ሐይቁ ሲመጡ እፎይታ ይሰማቸዋል። « በሐይቁ ዳር ዳር ሆቴሎች መኖራቸው መልካም ነው » የሚሉት አስተያየት ሰጪዋ፤ አልፎ አልፎ የሚያስደምጡት ሙዚቃ በሐይቁ ዳርቻ ላይ እፎይ ብሎ መቀመጥ የሚፈልግን ሰው ምቾት እንደሚነሳነው የገለጹት። « በሐይቁ ዙሪያ ያለው ተፈጥሮአዊ ትዕይነት ብቻ በራሱ በቂ ነው » ባይ ናቸው። ለከተማዋ ውበት አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል የመጀመሪያውን ስፍራ የሚይዘው የሐዋሳ ሐይቅ ደህንነቱን ለመጠበቅ « ተኝተን አናድርም » ይላሉ የከተማው ከንቲባ አቶ ዮ