የፍቼ ጫምባላላ በዓል የሲዳማ ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ ሊሆን ይገባል፤
የሲዳማ ዞን ከምድር ወገብ በስተሰሜን አካባቢ ይገኛል። በሰሜናዊ ምስራቅና በደቡባዊ ምስራቅ የኦሮሚያ ክልል በደቡብ ጌዲኦ ዞንና የኦሮሚያ ክልል፣ በምእራብ በኩል ደግሞ የወላይታ ዞን ያዋስኑታል። ዞኑ በሶስት የአየር ንብረቶች የሚካተት ሲሆን 30 በመቶ ደጋ፣ 60 በመቶ ወይና ደጋ፣ 10 በመቶ በቆላ ይሸፈናል። የዞኑ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 7 ሺ 200 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆን በ 19 የገጠር ወረዳዎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተዋቀረ ነው። በ 1999 ዓ . ም በተካሄደው የህዝብና የቤቶች ቆጠራ መሰረት በዞኑ የሚገኘው የሲዳማ ህዝብ ብዛት 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን እንደሚሆን ተገምቷል። የሲዳማ ብሄር በሰሜናዊ ምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ የኩሽ ቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል ተጠቃሽ ሲሆን በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ ነው። የሲዳማ ብሄር የራሱ የሆነ የጊዜ አቆጣጠር ቀመር ያለው ሲሆን ቀመሩን ተከትሎ የፍቼ የዘመን መለወጫ በዓል በድምቅት ይከበራል። የፍቼ በዓል የሚከበርበትን ቀን « አያንቶ » ( የተመረጡ አዛውንቶች ) ክዋክብት በጨረቃ ዙሪያ የሚያደርጉትን ኡደት በመቃኘት ይወስናሉ። በጎሳ መሪው ( ሞቴው ) ውሳኔ መሰረት የበዓሉ ቀን ከታወጀ በኋላ ሁሉም በየፊናው ዝግጅቱን ያጧጡፋል። በዓሉም እስከ ሁለት ሳምንታት ለሚደርስ ጊዜ በየአካባቢው በሚገኙ « ጉዱማይሌዎች » ( አደባባዮች ) በድምቀት ይከበራል። ጉዱማይሌ በዞኑ በሚገኙ መንደራት ሁሉ የሚገኝ ሲሆን ትልቅ ክብር የሚሰጠው ቦታ ነው። አራስ የመታረሻ ጊዜዋ አብቅቶ ከመውጣቷ በፊት ከልጇ ጋር በቅድሚያ የምታየው ጉዱማይሌውን ነው። ሙሽሮች ከሰርጋቸው ማግስት ጀምሮ ጉዱማይሌን ሳያዩ ወደአዲሱ ኑሯቸው አይቀላቀሉም። የሲዳማ ብሄር ተወላጆች እንደየእድሜያቸውና በ