የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰልፍ ክልከላ ቀጭን መስመር
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መስከረም 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ለሁለተኛ ጊዜ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በበርካታ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሰልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት ዙሪያ የሰጡት ምላሽ ግን አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤጥ እቁባይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረበችው ጥያቄ የሚከተለው ነበር፡- ‹‹የትግል እንቅስቃሴአቸውን አገር ውስጥ እያደረጉ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ጊዜዎች በተለያዩ ከተማዎች ከመንግሥት ምላሽ ይፈልጋሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ሰላማዊ ሰልፎችን አድርገዋል፡፡ ምንም እንኳን ሰልፎቹን አስመልክቶ በመንግሥት ኮሚኒኬሽን በኩል የተሰጡ መግለጫዎች ቢኖሩም ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች ‹ምላሽ ያሻቸዋል፣ አግባብነት አላቸው› ብለው መንግስትም በተለያየ መንገድ ከሚሰበስባቸው መረጃዎች የወሰዷቸው ጥያቄዎች አሉ ወይ›› ለጥያቄው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠው ምላሽ ለብዙዎች የሚያረካ ነበር ለማለት ያስቸግራል፡፡ ይልቁንም ምላሹ ሌሎች ተጨማሪ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስቷል፡፡ በመልሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን፣ መንግሥታቸው በጫና ሐሳቡን የሚቀይር እንዳልሆነ፣ ተመሳሳይ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ከተጠየቁ መንግሥት አንድ ቦታ ላይ እንደሚያቆመው፣ የፓርቲዎች መብዛት ሰልፉን እንዳበዛው፣ ሰልፉ የሚታወቀው ውጭ ባሉ የእቅዱ ባለቤቶች እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ሰላማዊ ሰልፍ እንደ ሕገ መንግሥታዊ መብት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ‹‹ተቃዋሚዎች ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሰጣቸው መብት እንጂ ማንም በችሮታ የሰጣቸው