‹‹የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ስድስት ዓመት ገለልተኛ ሆኖ ካገለገለ በኋላ ነፃ ሆኖ ሐሳቡን መግለጽ መቻል አለበት››
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የመጀመሪያው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ከሽግግር መንግሥቱ በኋላ በኢትዮጵያ በሦስት ዙር (ተርም) ሁለት ርዕሰ ብሔሮች [ፕሬዚዳንቶች] ተሰይመዋል፡፡ ላለፉት 12 ዓመታት በሥራ ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በ2005 ዓ.ም. የሥራ ዘመናቸው ያበቃል፡፡ በ2006 ዓ.ም. በመስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባዔ ሲከፈት ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት የሚያገለግሉ አዲስ ፕሬዚዳንት ይሰየማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወደተንጣለለው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ማን ሊገባ ይችላል የሚለው ጉዳይ እስካሁን ባይታወቅም፣ የተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የተለያዩ ሰዎችን ሰብዕና በመምዘዝ እየተነጋገሩ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲም በዚህ ጉዳይ ላይ መጠመዱ ተሰምቷል፡፡ ኢትዮጵያ ፓርላሜንታዊ ሥርዓት የምትከተል አገር ተደርጋ የኢፌዲሪ መንግሥት ሲመሠረት፣ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነው መንበሩን የተቆናጠጡት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ነበሩ፡፡ ከፕሬዚዳንትነታቸው ቆይታ፣ ከቤተ መንግሥት ሕይወትና ከቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አሿሿምና ተግባር ጋር በተያያዘ የአሁኑን የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶን ውድነህ ዘነበ አነጋግሯቸዋል፡፡ ሪፖርተር፡- የኢፌዲሪ መንግሥት ሲመሠረት የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት እርስዎ ነበሩ፡፡ የተመረጡበት ሒደት እንዴት ነበር? የተጠቆሙ ሰዎችስ ነበሩ? ዶ/ር ነጋሶ ፡- በ1987 ዓ.ም. ከምርጫው በፊት ነው የሆነው፡፡ ሒደቱ አሁን ተለውጦ ከሆነ አላውቅም፡፡ የዚያን ጊዜ በሥራ አስፈጻሚ ተነጋግረን ሦስት ሐሳቦች ቀረቡ፡፡ አንደኛ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ፣ ሁለተኛ ፕሮፌሰር ጀማል አብዱልቃድር [የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩ]፣ ሦስተኛ አም