ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ውግዘትና የመንግሥት ክርክር
በመስፍን መንግሥቱ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የገዛ ዜጎቹን መብቶች ያለገደብ የሚጥስና ሰብዓዊ መብት የሚጥስ እየተባለ ያልተከሰሰበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ መንግሥት በዜጎች ላይ ይፈጽመዋል በሚባለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዓለም አቀፍ ትኩረትን በሚመለከት የመጀመሪያ ምዕራፍ አይደለም፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የዜጎች ጅምላ ግድያዎችን ዓለም በከፍተኛ መገረም ተከታትሎ አውግዟቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም አገዛዛቸው በኢትዮጵያ የከፍተኛ ጭካኔና የመብት ጥሰት ዘመን ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባተረፈው ታዋቂነት ምክንያት የውግዘት ዒላማ ሆኖ አልፏል፡፡ የደርግ መውደቅ በኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የፍፃሜ ምዕራፍ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ ከኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተለይም ሒዩማን ራይት ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያኔ አዲስ የነበረውን የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት በማብጠልጠል ነበር የተቀበሉት፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት ይህ ሥራቸው ሆኖ ዘልቋል፡፡ ጋዜጠኞችን ከመንግሥት ጥቃት በመከላከል ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ድርጀቶችም የኢትዮጵያን መንግሥት በየጊዜው መክሰስ ሥራቸው ሆኗል፡፡ ከእነኝህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በተጨማሪ የአሜሪካ መንግሥት ውጭ ጉዳይ መሥርያ ቤትም በየጊዜው በሚያወጣው ዓመታዊ መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥትን በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፖለቲካ መብቶችን ማፈን ሳይከስ ያለፈበት ጊዜ የለም፡፡ አሁን አሁን የእነኚህን አካላት መግለጫዎች የታወቁ ዓለም አቀፍ መገናኛ ድርጅቶች በመቀባበል