በደቡብ ክልል ከ12ሺህ 400 በላይ የባዪ ጋዝ ተቋማት ግንባታ እየተከናወነ ነው
ሃዋሳ ሐምሌ 27/2005 በደቡብ ክልል በተጠናቀቀዉ በጀት አመት የ12ሺህ 415 የባዮ ጋዝ ተቋማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ውሃ ሀብት ቢሮ አስታወቀ ። የቢሮ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት ባለሙያ አቶ ጁሲ ጥላሁን ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የባዮ ጋዝ ተቋማቱ ግንባታ እየተካሄደ ያለዉ አማራጭ የሀይል አቅርቦትን ለህብረተሰቡ ለማዳረስ መንግስት በያዘው ፕሮግራም መሰረት ነዉ ። በተጨማሪ በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ የገጠር አካባቢዎች 193ሺህ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማሰራጨት ከ190ሺህ ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል ። የባዮ ጋዝ ተቋማቱ የግብርና ተረፈ ምርቶችን በማብላለት ከሚወጣዉ ጋዝ በርካታ ቤተሰቦችን የመብራትና የምግብ ማሰያ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አገልጠዋል ። በክልሉ አማራጭ የሃይል አቅርቦት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ በተደረገው ጥረት ባለፉት አመታት በተመሳሳይ በርካታ የገጠር ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታዉቀዋል ። ይህም ለማገዶና ለሀይል ፍላጎት እየተባለ የሚወድመውን የደን ሀብት ከመታደግ በሻገር የህብረተሰቡን የስራ ጊዜ ፣ ጉልበትና ወጪ ለመቆጠብ ከፍተኛ አስተዋጾኦ አድርጓል ብለዋል ። በደቡብ ክልል በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ታዳሽና አማራጭ የሀይል አቅርቦት በ2002 ከነበረበት 15 በመቶ ሽፋን ወደ 25 በመቶ ለማሳደግ ሰፋፊ ፕሮግራሞች ተነድፈው እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ። በበጀት አመቱ ለኢነርጂና ለማእድን ልማት ጨምሮ የሚስፈልገው አጠቃላይ የማስፈጸሚያ በጀት ከ19ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን በእቅዱ ላይ ተመልክቷል፡፡