አንድነት የፀረ-ሽብር አዋጁን ለማሰረዝ የ1ሚ. ሰዎችን ፊርማ ያሰባስባል
ዶ/ር ነጋሶ የመጀመሪያው ፈራሚ ሆነዋል “የአገሩን በሬ በአገሩ ሰርዶ እንጂ በውጭ ተቋማት መተማመንይቅር” - ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ከትላንት በስቲያ በይፋ የጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ የፀረ-ሽብር አዋጁን ማሰረዝ ዋነኛ አላማው እንደሆነ ገለፀ፡፡ ለዚህ ዓላማውም የአንድ ሚሊዮን ሰዎችን የድጋፍ ፊርማ (ፒቲሽን) በዕለቱ ማስፈረም የጀመረ ሲሆን የመጀመሪያው ፈራሚ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሆነዋል፡፡ ፓርቲው የፀረ-ሽብር ህጉን ለማሰረዝ ከሚንቀሳቀስባቸው ምክንያቶች አንዱ ህገ-መንግስቱን በእጅጉ የሚጥስና የኢትዮጵያን ዜጐች በማጥቃት የሚጀምር በመሆኑ ነው ብሏል - የህዝባዊ ንቅናቄው ኮሚቴ በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡ ፓርቲው “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” በሚል መሪ ቃል የጀመረው የሶስት ወር ንቅናቄ የአንድ ሚሊዮን ህዝቦችን ድምፅ በማሰባሠብ የአገሪቱን ዜጐችና ተቋማትን በማጥቃት፣ በሀይማኖት ጣልቃ በመግባት፣ ከአባትና እናት የተወረሠን ንብረትና ሀብት በሽብርተኝነት ስም የሚገፈውን አዋጅ ለማሰረዝ ጥረት እናደርጋለን፤ ወደ ክስም እንሄዳለን” ብሏል፡፡ “ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ካላት ተፈጥሯዊ ሀብትና መሠል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የፀረ-ሽብር ህግ አያስፈልጋትም ማለት እንዳልሆነ የገለፁት የንቅናቄው ኮሚቴ አባል አቶ ትዕግስቱ አወል፤ አሁን ስራ ላይ ያለው የፀረ ሽብር አዋጅ ግን ሰዎችን እና ተቋማትን የሚያጠቃ ነው ብለዋል፡፡ ከተጠቁት ተቋማት ውስጥ አንድነትና መድረክ ዋነኞቹ እንደሆኑ፣ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ሰዎችም የዚሁ አዋጅ ሠለባ መሆናቸውን፣ እንዲሁም ከህገ መንግስቱ ጋርም በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚቃረን ትኩረት አድርገንበታል ሲሉም አክለዋል፡፡ “ምንም እንኳን በፍትህ ተቋማቱ ላይ ያለን እምነት የተሸ