የጦቢያ መንግስት ቆሞ የሚሄደው “ምቀኛ አታሳጣኝ” በሚለው ፀሎት ነው!
Written by ኤልያስ ምቀኞች ቢበዙልን እኮ ባለ3 ዲጂት እድገት እናስመዘግብ ነበር ! አንዳንዴ የአባቶችን ተረትና ምሳሌ እንዲሁም ብሂል ዝም ብሎ ማጣጣል “ፌር” አይመስለኝም። አንዳንድ ቀለም የዘለቃቸው የጦቢያ ምሁሮችና ዘመናይ ነን ባዮች ግን እነዚህን ሥነ ቃሎች ለድህነታችንና ኋላ ቀርነታችን ሰበብ አድርገው ያቀርባሉ፡፡ አላወቁም እንጂ ጦቢያችን ከእነመንግስቷ ቆማ የምትሄደው በእነዚህ ወርቃማ አባባሎች እኮ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር---ከእነዚህ ምሁር ነን ባዮች እኮ የጥንቶቹ አባቶቻችን በብዙ ነገር ሺ ጊዜ ይበልጧቸዋል፡፡ እናም “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እላቸዋለሁ - የአባቶቻችንን ብሂሎች የሚተቹትን የጦቢያ ምሁሮች፡፡ ይሄን ግሳፄ የምሰነዝረው ግን ዝም ብዬ አይደለም፡፡ ብሂሎቹ ለጦቢያ የህልውና መሠረት መሆናቸውን ስለደረስኩበት ነው፡፡ ለዛሬ ልዩ ትኩረት አድርገን የምንፈትሸው ከጥንት የአባቶች አባባል ከወረስናቸው ሥነቃሎች መካከል “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለውን ወርቃማ ብሂል ነው፡፡ እውነቴን ነው የምላችሁ --- የጦቢያችን ህልውና የተመሰረተው ሙሉ በሙሉ በእዚህ ብሂል ላይ ነው፡፡ ብታምኑኝም ባታምኑኝም “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለው ሥነ ቃል ባይኖር ጦቢያችን አትኖርም ነበር፡፡ ጥናቴ እንደሚጠቁመው፤ የአበሻ ዘር ምቀኛ ያጣ ዕለት መኖር ያቆማል (አሳዛኝ ቢመስልም ሃቅ ነው!) በአጠቃላይ የዕድገታችን በሉት የስልጣኔያችን ወይም በኢህአዴግ ቋንቋ የህዳሴያችን መሰረቱ “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለው መሪ ሥነ ቃል ነው፡፡ አበሻ ሲፀልይ “ምቀኛ አታሳጣኝ” ይላል ሲባል አልሰማችሁም? ቀልድ ከመሰላችሁ እንደኔ ተሸውዳችኋል፡፡ ፈፅሞ የማያጠራጥር ሃቅ መሆኑን እኔ ላረጋግጥላችሁ እችላለሁ - በመረጃም በማስረጃም፡፡ እንኳን ዜጐች ራሳቸው ፖለቲከኞችም ከዚ