አስደንጋጮቹ የሙስና ምልክቶች
በአማን ንጋቱ በሁሉም መሥሪያ ቤቶች ግድግዳ፣ በር፣ የማስታወቂያ ሰሌዳ አንዳንዴም በውስጥ ክፍሎች የተደረቱ ጽሑፎች ይታያሉ፡፡ ቢነበብም ባይነበቡም አንዱ በሌላው ላይ እየተደራረቡ ጽሑፎች ይለጠፋሉ፡፡ አሥራ ሦስት ገደማ ፍሬ ነገሮችን የያዘው “የሥነ ምግባር ደንብ መርሆዎች” የሚለው ርዕስ በየቦታው ጎልቶ ይታያል፡፡ እንደ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ ግልጽነት፣ ሐቀኝነት ያሉት የአብዛኛዎቹ መርሆዎች ማጠንጠኛቸው፣ “ሙስና፣ ጉቦና መድልኦን መፀየፍ” እንደሆነ ከጽሑፎቹ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይሁንና መርሆዎቹ ከወረቀት ጌጥነት ባለፈ ያመጡት ለውጥ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡ የለውጥ ሥራዎች ተግባራዊነት፣ የድርጅት ግምገማ መጠናከር (ከብዛቱ አንፃር ትግል ደክሟል የሚሉ የኢሕአዴግ ሰዎች አሉ) የሕጉ መሻሻልና የማስቀጣት አቅም መጨመር ዕውን ሙስናን ቀንሶታል ወይስ ተባብሷል በማለት የሚጠይቁ በዝተዋል፡፡ አቶ ጀማል ያሲን የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህር ናቸው፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ቢቀረፅም ሳይሠሩ የመክበር ዝንባሌው ሥር የሰደደ በመሆኑ በቀላሉ የሚነቀል ነቀርሳ አይደለም ይላሉ፡፡ “ሲሾም ያልበላ…” ከሚለው ተረት “የኮንትሮባንድ ፈታሽ” ወይም “የመርካቶ ትራፊክ ያድርግህ” እስከሚለው ምርቃት ድረስ ሳይሠሩ የመክበር አስተሳሰብ የተንሰራፋ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ቀስ በቀስ እየገነነ የመጣው ከመንግሥታዊ መዋቅር ባለፈ በሃይማኖት ተቋማትና በሲቪክ ማኅበራት ሳይቀር የሚታይ ጉቦ የመጠየቅ ፍላጎት ምንጩም ይኼው ነው፡፡ ዛሬ በትምህርትና በሕክምና ተቋማት ብቻ ሳይሆን በቀብር ሥፍራ ሳይቀር ሕግ ከሚያውቀው ክፍያ ውጪ “መወሸቅ” ተለምዷል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ፣ የነፃ ገበያና ኮሚሽን (ኤጀንት) ከሥራ መስክነት