የኮንዶምኒዬም ልዩ ኮታ ለመንግስት ሰራተኞች! ልዩ ኮታው… ለፓርቲ አባላት መሆኑ ነው?
ቢሆንስ ምን ችግር አለው? “ህዝብ” ናቸዋ! ችግር ቢኖረውስ የት ይደረሳል? ዝም ነው! ብዙዎቻችን ፈቅደን ያስጀመርነው አይደል! የመንግስት ሰራተኞች ከሌላው ዜጋ የበለጠ የኮንዶምኒዬም ኮታ እንደሚመደብላቸው ባለፈው ቅዳሜ እለት ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲናገሩ በጣም ነበር የገረመኝ። የመንግስት ሰራተኞች ከሌላው ዜጋ በምን ይበልጣሉ? በርካታ የፓርቲ አባላትን ስላሉበት ነው ልዩ እንክብካቤ የሚደረግላቸው? አይን ያወጣ አድልዎ መስሎ ስለሚታየኝ ነው የተገረምኩት፤ የደነገጥኩት። ረጋ ብዬ ሳስበው ግን፤ ለካ ያን ያህልም አስገራሚ አይደለም። “ኧረ ጉድ!” የሚል ሰውም አላጋጠመኝም። ደግሞም አዲስ የተፈጠረ ነገር የለም። የመንግስት ችሮታ፣ ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ የአገራችን ባህል ነው። የድሮ ነገስታት፣ በነሱ ፊት ከሌላው ሰው በልጦ ለታያቸው “አገልጋይ”፣ ልዩ ድጋፍ ያደርጉ ነበር። “አገር ያቀና”፣ “በታማኝነት ያገለገለ”፣ “በትውልድ ሃረጉ የከበረ”፣ “በእምነቱ የፀና” … በሚሉ የተለያዩ ሰበቦች መሬት ይሰጡታል፤ መተዳደሪያ ገቢ የሚያገኝበት ግዛት ይሸልሙታል። እንደፈቃዳቸውም፣ ላሰኛቸውና ስሜታቸውን ለነካው ሰው ወይም ተወዳጅነትን ያስገኛል ብለው ሲያስቡ ለመንገደኛ ሁሉ ምፅዋት ለመስጠት እጃቸውን ይዘረጋሉ። አልያም፣ “ስጠው” ብለው የግምጃ ቤት ተቆጣጣሪውን ያዝዙታል። አልያማ ንጉስነታቸውና መንግስትነታቸው ምኑ ላይ ነው? በእርግጥ ነገሥታት መሬት ጠፍጥፈው አይሰሩም። ማሳ አርሰውና ብረት ቀጥቅጠው መተዳደሪያ ገቢ አያመርቱም። ግን ችግር የለውም። ያው፤ ከአንዱ ዜጋ መሬት ነጥቀው ለሌላው ይሰጣሉ። ዜጎችን እያስገበረ መተዳደሪያ ገቢ እንዲያገኝ፣ ከወንዙ ማዶና ከተራራው ወዲህ ያለውን ግዛት ሰጥቼሃለሁ ይሉታል። ትንሽ ቆንጥረው ለተወሰኑ ዜጎች በምፅዋት ያከፋፍላሉ። “ለተ