የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ የካቢኔ አደረጃጀት እያነጋገረ ነው
- ካቢኔው በሕገ መንግሥቱ መሠረት አንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ይኖረዋል - የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ያላቸው ሁለት ባለሥልጣናት ተሹመዋል - አዲሱ አደረጃጀት ከሌሎች ሕጐች ጋር ተቃርኖ አለው እየተባለ ነው በዮሐንስ አንበርብር የሥራ አስፈጻሚውን ከፍተኛ ሥልጣን በማግኘት አገሪቱን መምራት ከጀመሩ ሁለት ወራት ከቀናት ያስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ ካቢኔያቸውን በአዲስ መልክ እንዳደራጁ አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችንና የሌሎች ሚኒስትሮችን ሹመት አፀድቀዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ የካቢኔ አደረጃጀትም መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት (ካቢኔ) በሕገ መንግሥቱና በመመሥረቻ አዋጁ የተጣለበትን ኃላፊነቶች በብቃት ለመወጣትና የአስፈጻሚነት ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ ለማድረግ፣ እንደ አዲስ በሦስት ዘርፎች መዋቀሩ አስፈላጊ መሆኑን ለፓርላማው አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲፕሎማሲ፣ የደኅንነት፣ የመከላከያ እንዲሁም ከፍተኛና ግዙፍ (ሜጋ) ፕሮጀክቶችን በቀጥታ እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ አስፈጻሚው የሚከታተላቸውን ተግባራት በብቃት ለመምራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሦስት ዘርፎች እንዲዋቀር መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ማኅበራዊ ጉዳዮችን፣ መልካም አስተዳደርና ረፎርምን፣ ፋይናንስና ኢኮኖሚን የሚመለከቱ ሦስት የሥራ ዘርፎች በአዲሱ የካቢኔ መዋቅር የተፈጠሩ ሲሆን፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የማኅበራዊ ዘርፉን የሚመሩ መሆኑ ታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና የካቢኔ ጉዳዮች ቢሮን በሚኒስት