‹‹ሐዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ……
በሔኖክ ረታ ኅዳር መባቻ ማለዳ ላይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰበሰበው የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን ሴንተር (ኤምሲሲ) ሠራተኛ በድርጅቱ አማካይነት የተሰናዳለትን የሽርሽር ጉዞ ለመጀመር በንቃት ቦታ ቦታውን ይዟል፡፡ ሁለተኛውን የሚዲያና የኪነጥበብ ባለሞያዎች የእግር ኳስ የዋንጫ ውድድርን በሦስተኛነት በማጠናቀቁ ነበር ከሌሎቹ አሸናፊዎች ጋር በመሆን ይህን የጉዞ ዕድል ያገኘው፡፡ ከማለዳው አንድ ሰዓት ላይ ወደ ሐዋሳ ከተማ የተጀመረው ጉዞ ከአዲስ አበባ በስተምሥራቅ 30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ዱከም ከተማ ላይ የቁርስ ቆይታ ነበረው፡፡ በቀድሞው አትሌት ወርቁ ቢቂላ ሆቴል ቁርስ የተመገቡት የኤምሲሲ አባላት ከቀድሞው አትሌት ጋር ትውውቅና የተወሰነ ቆይታ የማድረግ አጋጣሚም ነበራቸው፡፡ ቢሾፍቱንና ሞጆን በተከታታይ አልፎ በግምት አምስት ሰዓት ገደማ ላይ የካስቴል ወይን እርሻና ፋብሪካ ለመጎብኘት አዳሚ ቱሉ ወረዳ ደርሷል፡፡ በዘመናዊ ማሽኖችና ቴክኖሎጂዎች የተገነባው የወይን መጥመቂያ ፋብሪካ ከተንጣለለው የወይን እርሻ በሰው ኃይል አማካይነት የተለቀመውን ፍሬ በረዥም የጊዜ ሒደት ውስጥ የሚፈለገውን የወይን ጣዕም አቀነባብሮ ለገበያ የሚያቀርብ ግዙፍ የወይን እርሻና ማምረቻ እንደሆነ በድርጅቱ የምርት ክፍል ባለሞያ የሆኑት አቶ ዳዊት ገብሬ ለጎብኚዎቹ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡ እንደ ብረት ምጣድ በጋለው የመኪናው ጣራና ግድግዳ በኩል እየገባ የሚፋጀው ጠራራ ፀሐይ ጎብኚዎችን በከፍተኛ ሙቀት ቢፈትንም በጨዋታና በሙዚቃ የተዋዛውን ጉዞ ሊያደበዝዘው አልቻለም ነበር፡፡ መቂ፣ ዝዋይንና አርሲ ነገሌ ከተሞችን በፈታኝ የፀሐይ ሙቀት የጨረሰው ጉዞ ሰባት ሰዓት ገደማ ላይ ከመዳረሻዋ የሐዋሳ ከተማ በ23 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ብቻ ቀደም ብላ የምትገኘውን ሞቅ ያለች