ግልጽነትና ተጠያቂነት የመልካም አስተዳደር ወሳኝ መሣሪያዎች ናቸው
ሕዝብም መልካም አስተዳደር እፈልጋለሁ ይላል፡፡ መንግሥትም መልካም አስተዳደርን ማስፈንና ማረጋገጥ ራዕዬ፣ ዓላማዬና ዕቅዴ ነው ይላል፡፡ በዚህ ላይ ልዩነት የለም፡፡ በአባባል፣ በፍላጎትና በምኞት ደረጃ፡፡ መልካም አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ ግን የግድ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን በተግባር ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ከሌለ መልካም አስተዳደር አይኖርም፣ አይሰፍንም፡፡ ግልጽነት ሲባል ትርጉሙ ‹‹ግልጽና ግልጽ›› ነው፡፡ በሕዝብ ተመርጫለሁ የሚል መንግሥት ውክልና ሰጥቶ፣ መርጦ ለሥልጣን ላበቃው ሕዝብ የሚሠራውንና የሚያስበውን በግልጽ ማሳወቅ አለበት፡፡ ሕዝብ መንግሥትን እዚህ ጋ ተሳስተሃል፣ እዚህ ጋ አጥፍተሃል፣ እዚህ ጋ ጥሩ ሠርተሃል፣ እዚህ ጋ እንዲህ ብታደርግ ይሻላል በማለት ሕገ መንግሥቱ የሰጠውን መብት ተጠቅሞ ሐሳብ ለመስጠት፣ ሂስ ለማቅረብና ድጋፉን ለመግለጽ መንግሥት የሚያከናውነውን ሁሉ በግልጽ ሊያውቀው ይገባል፡፡ መንግሥት ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥታችን ግልጽነትን ይደግፋል፡፡ ሁሉም ነገር ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆን የሚያዝና የሚደነግግ ሕግም አለን፡፡ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፡፡ በሕገ መንግሥትና በሕግ በኩል በአገራችን ግልጽነት እንዳይኖር የሚያደርግ አንዳችም ነገር የለም፡፡ በተግባር ግን ግልጽነት እየተዳከመ ነው፡፡ በተግባር ግን ቢሮክራሲው የሚጠቅመውን ይናገራል፤ የማይጠቅመውንና የሚያጋልጠውን ይደብቃል እንጂ ግልጽነት (ትራንስፓረንሲ) እውን ሊሆን አልቻለም፡፡ ለመልካም አስተዳደር ትልቅ የተደቀነ እንቅፋት የሆነው የግልጽነት አለመኖር ሆኗል፡፡ ተጠያቂነትን (አካውንተቢሊቲ) በሚመለከትም ሕገ መንግሥታችንና ሕጎቻችን የሚደግፉትና የሚያበረታቱት ናቸው፡፡ በተግባር ግን ተጠያቂነት እየጠፋ ነው፡፡ ቢሮክራ