“መልካም አስተዳደርን ያላካተተ ልማት ልማት አይባልም”
በምሕረት ሞገስ ኢትዮጵያ በልማቱ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ታስመዝግብ እንጂ ዴሞክራሲን በማስፈን ወደኋላ እንደቀረች የተለያዩ የሰብአዊ መብትተሟጋች ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ኢሕአዴግም ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንሥቶ ትችት ሲሰነዘርበት የቆየው ዴሞክራሲን ማስፈን ባለመቻሉ ነው፡፡ መንግሥት ዴሞክራሲን ለማስፈን ብዙ ትኩረት ባለመስጠቱ የበላይና የበታች እንዲኖር፣ ፍትሕ እንዲዛባ በአጠቃላይም የመልካም አስተዳደር እጦት በአገሪቷ እንዲስፋፋ አድርጓል በሚልም ይተቻል፡፡ አቶ አሰፋ አደፍርስ በአሜሪካ ለ39 ዓመታት ኖረዋል፡፡ በኢትዮጵያ በልማቱ ዘርፍ ከተሰማሩም ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ በሥራ አጋጣሚ የሚያስተውሉት የመልካም አስተዳደር እጦት ግን አገሪቷን ወደኋላ የጐተተ፤ እሳቸውና ሌሎች ባለሃብቶችም የተሰማሩባቸውን የተለያዩ የልማት ዘርፎች ከሚፈለገው ደረጃ እንዳይደርስ ማነቆ የሆነ ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት በተንሰራፋበት ሁኔታ የሚታይ የኢኮኖሚ ዕድገትም በሕዝቡ ኑሮ ላይ ለውጥ እንደማያመጣም ይናገራሉ፡፡ ከሚኖሩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በአገሪቱ ለውጥ ማየታቸውን፤ ሆኖም ለውጡ መሳጭ አለመሆኑን የሚናገሩት አቶ አሰፋ “አገር ውስጥ ያለውም ሆነ ከውጭ የሚመጣ ባለሀብት ሕንጻ ሊሠራ ይችላል፡፡ ሕንጻ ስለተደረደረ ግን ልማት ለማ ማለት አይደለም፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከሕዝቧ በላይ ሊያስተዳድር የሚችል ሀብት አላት፡፡ ሆኖም በየመንገዱ የሚለምን እናያለን፣ ልጃቸውን አዝለው የሚበሉት የሚጠይቁ ይታያሉ፡፡ ይህ የሚሆነው ከመልካም አስተዳደር እጦት በሚመነጭ ችግር ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን ያላካተተ ልማት ልማት አይባልም፤” ብለዋል፡፡ በመልካም አስተዳደር እጦት ላይ ያለው ችግር አሁን የመጣ ሳይሆን የቆየ ሊሆን ይችላል፡፡ በደርግ ጊዜ ከነበረው ጋ