የኢሕአዴግ ታጋዮች ጡረታ ትግሉን ከተቀላቀሉበት ጊዜ ጀምሮ ሊሰላ ነው
የቀድሞውን ወታደራዊ አገዛዝ የመገርሰስ ትግል ውስጥ የተሳተፉና በአሁኑ ወቅት በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ የሚገኙ የቀድሞ ታጋዮች ጡረታ (ማኅበራዊ ዋስትና) ትግሉን ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶ እንዲሰላ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በጻፈው ደብዳቤ አሳሰበ፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለመንግሥት ተቋማት የተሰራጨው ደብዳቤ ከሰኔ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነና ይህም ማለት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤውን ያሰራጨው በሕግ ላይ ተመሥርቶ ይሁን አይሁን በእርግጠኝነት ለመናገር እንደማይችሉ የሪፖርተር ምንጮች የገለጹ ቢሆንም፣ ምናልባት ለሕዝብ ይፋ ያልሆነ መመርያ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ሊሆን እንደሚችልና ደብዳቤውም በዚህ ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንን መረጃ በመንተራስ ሪፖርተር አንዳንድ በመንግሥት ሥራ ላይ የተሰማሩ የቀድሞ ታጋዮችን ለማነጋገር የሞከረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በአባልነት እያገለገሉ ያሉ ይገኙበታል፡፡ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት እነዚሁ የምክር ቤቱ አባላት የመረጃውን ትክክለኝነት ያረጋገጡ ሲሆን፣ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ ባቀረበው ጥሪ መሠረት ማንነታቸውን የሚገልጽ፣ ትግሉን የተቀላቀሉበትን ወቅትና በአሁኑ ጊዜ የሚያገለግሉበትን የመንግሥት ተቋምና ሌሎች ጉዳዮችን በተዘጋጀ ቅጽ ላይ መሙላታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህንን ቅጽ ከሞሉ በኋላ ደግሞ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ከሰሞኑ በድጋሚ ማስታወቂያ እንዳወጣ፣ ማስታወቂያውም የተሞላውን ቅጽ ተንተርሶ የመንግሥት ሠራተኞች ማ