የቡና ዋጋ ወሰን ሙሉ ለሙሉ ተነሳ
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቡና መገበያያ የዋጋ ወሰንን ከትናንት በስቲያ ገበያ መዝጊያ ዋጋ አኳያ ወደ ላይና ወደ ታች የአምስት በመቶ ጭማሪና ቅናሽ እንዲያሳይ በማድረግ ሲያገበያይበት የነበረውን አሠራር ላልተወሰነ ጊዜ ማንሳቱን አስታወቀ፡፡ የምርት ገበያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር እሌኒ ገብረ መድኅን ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የዋጋውን ወሰን ማንሳት ያስፈለገው በኒውዮርክ ዓለም አቀፍ ገበያ ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ የመጣው የቡና ዋጋ፣ ባለፈው ሐሙስ ዕለት በፓውንድ (ግማሽ ኪሎ ገደማ) አንድ ዶላር ከሰባ አምስት ሳንቲም የሆነ ዝቅተኛ ዋጋ በማስመዝገቡ የዋጋ ወሰኑን ሙሉ ለሙሉ ማንሳት አስፈልጓል፡፡ የዓለም የቡና ዋጋ እስኪስተካከል ድረስ የዋጋ ወሰኑ ሙሉ ለሙሉ ተነስቶ እንደሚቆይ የገለጹት ዶክተር እሌኒ፣ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች የቡና ዋጋ መው ረዱን የማይቀበሉት ከዚህ ቀደም የተሻለ ዋጋ ለማግኘት አስበው በእጃቸው ያቆዩት ቡና ይበልጥ ዋጋው ሲወርድ ለኪሳራ ስለሚያጋልጣቸው ነው ብለዋል፡፡ ይህም ሆኖ አቅራቢዎች በግድ ሽጡ እንዳልተባሉ ገልጸው፣ ምርቱን በእጃቸው ከማቆየት ይልቅ ግን እንዲህ ያለ ያልታሰበ የዋጋ ማሽቆልቆል እንዳይከሰት በእጃቸው ያለውን ቡና ቶሎ ለገበያ እንዲያቀርቡ መክረዋል፡፡ ከሦስት ወራት በፊት የቡና ዋጋ እስኪጨምር ድረስ ምርቱን በእጃቸው ይዘው ሲጠባበቁ የነበሩ አቅራቢዎች የዋጋው መውረድ እንደጎዳቸው ገልጸው፣ አምና በፓውንድ ሦስት ዶላር ያወጣ የነበረው ቡና ባለፈው ወር ወደ ሁለት ዶላር ሊወርድ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ያላቆመው የዋጋ ማሽቆልቆል ከሁለት ሳምንት በፊት የኒውዮርክ ገበያ ዋጋው ወደ አንድ ዶላር ከዘጠና ሊወርድ መቻሉን፣ ባለፈው ሐሙስ ደግሞ ብሶበት አንድ ዶላር ከሰባ አምስት ሳንቲም ማውጣቱን ይገልጻሉ፡፡ በአንፃሩ በምርት