ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአየር ንብረት ለውጥና በምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረ የምርምርና የትምህርት መርሀ ግብር መጀመሩን አስታወቀ

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በአየር ንብረት ለውጥና በምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረ የምርምርና የትምህርት መርሀ ግብር መጀመሩን አስታወቀ የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከጀርመኑ ሆኸንየም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በአየር ንብረት ለውጥና በምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረ የምርምርና የድህረ ምረቃ ትምህርት መርሃ ግብር መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ በምግብ ዋስትና ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖና መፍትሄዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ አበበ እንደገለጹት፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ጥረት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ተግዳሮት እየገጠመው ነው።
"ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሰፊ ጥናትና ምርምር ማድረግና በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት ያስፈልጋል" ብለዋል።
ለእዚህም የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከጀርመኑ ሆኸንየም ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የአየር ንብረት ለውጥ በምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅዕኖ ለመፍታት የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለጻ በፕሮጀክቱ 14 የምርምር ሥራዎች የሚካሄዱ ሲሆን በዩኒቨርሲቲዎቹ 12 ባለሙያዎች የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርት እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ስንታየሁ ይግረም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2030 ከተያዙ 17 ዘላቂ የልማት አጀንዳዎች መካከል ሰባቱን ለማሳካት የተቀረጸ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በምግብ ዋስትና፣ በአየር ንብረት ለውጥና በትምህርት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን የገለፁት አስተባባሪው በጀርመን መንግስት በተመደበ በጀት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በጀርመን ሆኸንየም ዩኒቨርሲቲ በአየር ሁኔታ ትንበያ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እየሰሩ ያሉት አቶ ማርቆስ ቡዱሳ የአየር ንብረት ለውጡ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ቀድሞ ለማወቅና ለመከላከል የሚረዳ ምርምር ለማካሄድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የሚያካሂዱት የምርምር ሥራም ኢትዮጵያን ጨምሮ ኢኮኖሚያቸው በግብርና ላይ ለተመሰረተ አፍርካ ሀገራት ጠቀሜታ እንደሚኖረው አመላክተዋል።
እንደ አቶ ማርቆስ ገለጻ በሃዋሳና ሆኸንየም ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የተፈጠረው የትብብር ስምምነት የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር ለመፍጠር እገዛ እያደረገ ነው። 
በጀርመኑ ሆኸንየም ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በመማር ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ቅድስት ወልደጊዮርጊስ ናቸው።
በኢትዮጵያ በሚገኙ 50 የተለያዩ የገብስ ዝርያዎች ላይ የአየር ንብረት የመቋቋም አቅማቸውን ለመለየት የሚያስችል ምርምር አያካሄዱ መሆናቸውን ገልፀዋል ።
እንደ ወይዘሮ ቅድሰት ገለጻ ምርምር እየተደረገባቸው ያሉት የገብስ ዝርያዎች በምርታማነታቸውና በንጥረ ነገር ይዘታቸው የተመረጡ ናቸው።
በምክክር መድረኩ ላይ የሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራማሪዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥ በምግብ ዋስትና ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ የሚያሳዩ የተለያዩ የምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር