በደቡብ ክልል የእንሰት አጠውልግ በሽታን የመከላከል ሥራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ

ዲላ መስከረም 26/2010 በደቡብ ክልል የእንሰት አጠውልግ በሽታን ትኩረት ሰጥቶ መከላከል ካልተቻለ ሰብሉ ከምርት ውጭ የሚሆንበት ደረጃ ሊከሰት እንደሚችል የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አሳሳበ።
ኢንስቲትዩት በተቀናጀ የእንሰት አጠውልግ በሽታ ቁጥጥርና መከላከያ ዘዴዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ትላንት በዲላ ከተማ አካሂዷል፡፡
በኢኒስቲትዩቱ የሰብል ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር አግደው በቀለ እንደገለፁት፣ በክልሉ ከደቡብ ኦሞ፣ ቤንች ማጂና ሰገን ሕዝቦች ዞኖች ከሚገኙ የተወሰኑ አካባቢዎች በስተቀር ሁሉም ዞኖች እንሰት አብቃዮች ናቸው ፡፡
ሰብሉ በሚበቅልበት ሁሉም አካባቢዎች የእንሰት አጠውልግ በሽታ ወቅት ጠብቆ እየተቀሰቀሰ በሰብሉ ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንን ተናግረዋል።
በእዚህም በሽታው ከማሳ ወደ ማሳ እየተስፋፋ መምጣቱንና ክስተቱ በስፋት በሚታይባቸው አካባቢዎች ሰብሉ ሙሉ ለሙሉ ከምርት ውጭ የሆኑባቸው ማሳዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸውን ጠቁመዋል ።
ይህም የእንሰት ተክል ቀስ በቀስ ከምርት ሂደት እየወጣና የአርሶአደሩም ተጠቃሚነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንዲመጣ ማድረጉን  አስረድተዋል፡፡
ዶክተር አግደው እንዳሉት፣ በበሽታው መንሰኤና መከላከያ ዜዴዎች ላይ ሕብረተሰቡ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ ከመሆኑ ባለፈ ተክሉ ምርታማ እንዲሆን እንደ ሌሎች ሰብሎች ብዙ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት አይደለም።
በሽታውን በመከላከል አርሶአደሩ ከእንሰት ማግኘት ያለበትን ጥቅም ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላት ከሌሎች ሰብሎች እኩል ለእንሰት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"ለእዚህም በየደረጃው የሚገኝ አመራርን ጨምሮ ባለድርሻ አካላትና አርሶአደሩን በማንቀሳቀስ የተቀናጀ የመከላከል ሥራ ሊሰራ ይገባል" ብለዋል ።
በመድረኩ ላይ ስለ በእንሰት ተከል ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት በሃዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል የዕፅዋት በሽታ ባለሙያ ዶክተር ፍቅሬ ሀንድሮ  በሽታው በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
አርሶአደሩ ከዚህ በፊት ዘልማዳዊ በሆነ መንገድ በበሽታው የተጠቃ እንሰትን በማስወገድ የመከላከል ሥራ ሲሰራ ቢቆይም የመከላከሉ መንገድ ጥንቃቄ የተሞላበት ባለመሆኑ በሽታው በድጋሚ ወደ መማሳው ይዛመት እንደነበር አመልክተዋል።
ማዕከሉ የደረሰበርት አዲስ የመከላከያ ዘዴ ከነባር ባህላዊ አሰራር ጋር የተጣመረ እንደሆነ በጥናቱ የጠቆሙት ዶክተር ፍቅሬ፣ በሙዝ አብቃይ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ውጤታማ መሆኑን ገልፀዋል።
አርሶአደሩ ባለው የእርሻ መሳሪያ በበሽታው የተጠቃውን እንሰት ካስወገደ በኋላ በመቅበርና ያስወገደበትን መሳሪያ በኬሚካል በማጠብ አሊያም በእሳት በመለብለብ በዘላቂነት መከላከል እንደሚችል አስረድተዋል ፡፡
የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዝናቡ ወልዴ በበኩላቸው፣ በዞኑ 37 ሺህ 236 ሄክታር መሬት ላይ እንሰት እንደሚለማ ተናግረዋል ።
ተክሉ ለዞኑ ህዝብ የምግብ ዋስትናን ከመጠበቅ ባለፈ በኢኮኖሚና ባህላዊ እሴትነቱ የጎላ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል።
በሽታው የሚዛመተበት ሁኔታ ከወቅት ወቅት እንደሚለያይ ጠቁመው፣ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በዞኑ በ22 ሄክታር ማሳ ላይ ጥቃት ማድረሱን ለአብነት ጠቅሰዋል።
"እስካሁን በበሽታው ዙሪያ ትኩረት ሰጥተን አልሰራንም፤ በቀጣይ እስከ አርሶአደሩ ድረስ ንቅናቄ በመፍጠር ከሌሎች ሰብሎች ባልተናነሰ መልኩ ትኩረት ሰጥተን የተቀናጀ የመከላከል ሥራ እንሰራለን" ብለዋል ፡፡
የወናጎ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አድሉ ታደሰ በበኩላቸው መድረኩ ከዚህ በፊት በበሽታው ምንነት፣መከላከያ መንገዶችና ቁጥጥር ላይ የነበረብንን ክፍተት እንድንመለከት አድርጎናል" ሲሉ ተናግረዋል ።
በመድረኩ በእንሰት አጠውልግ በሽታ መንስኤ፣ መከላከያ ዘዴዎችና በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎች ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ምንጭ፦ ኢዜኣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር